በአፍሪካ ዋንጫው ለመጀመሪያ ጊዜ የምታሳተፈው ምዕራብ አፍሪካዊቷ ጊኒ ቢሳው በሃገሯ አሰልጣኝ ከሚመሩ አራት የአፍሪካ ዋንጫ ቡድኖች መካከል ብትሆንም አንድም ተጫዋች ከሃገር ውስጥ ሊግ ያላካተተች ብቸኛዋ ሃገርም ጭምር ናት፡፡
ጊኒ ቢሳውን ለአፍሪካ ዋንጫው ታልፋለች ብሎ ያሰበ አፍሪካ እግርኳስ ተከታታይ ማግኘት ይከብዳል፡፡ ዛምቢያ እና ኮንጎ ብራዛቪልን የጣለችው ጊኒ ቢሳው 2016ን በስኬት አጠናቅቃለች፡፡
ብሄራዊ ቡድኑ ወደ ጋቦን ሲያቀና በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ጊኒ ቢሳዊያን ወደ ርዕሰ መዲናዋ ቢሳው መንገዶች ወጥተው ሸኝተዋቸዋል፡፡ የህልም የሚመስለው ጉዞ አሁን ላይ አፍሪካ ዋንጫው ላይ አድርሷቸዋል፡፡ እምብዛም ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣቸው ሃገራት ውጤት ሲያመጡበት በማይታየው አፍሪካ ዋንጫ ጊኒ ቢሳው የተሻለ ነገር ለማሳየት ትሞክራለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ብዛት – 0
ውጤት፡ –
አሰልጣኝ፡ ባሲሮ ካንዴ
ጊኒ ቢሳው በምድብ አንድ ከአዘጋጇ ጋቦን፣ ካሜሮን እና ቡርኪናፋሶ ጋር ተመድባለች፡፡ በ2016 መጀመሪያ ፖርቹጋላዊውን ፓውሎ ቶሬስ ተክተው የጊኒ ቢሳው የአሰልጣኝነት ወንበር የጨበጡት ባሲሮ ካንዴ ማንም ባልጠበቀው ሁኔታ ሃገራቸውን በታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ ወደ አፍሪካ ዋንጫው አሳልፈዋል፡፡ ከስፖርቲግ ክለብ ቢሳው ጋር 9 ግዜ ቻምፒዮን የቻሉት የ49 ዓመቱ ካንዴ ከምድቡ ማለፍ ተቀዳሚ አላማቸው እንደሆነ ለተለያዩ የፈረንሳይ ሚዲያዎች ከወራት በፊት ሲገልፁ ነበር፡፡ የጊኒ ቢሳው መሪዎች ለእግርኳስ ያላቸው አስተሳሰብ መለወጥ ሃገሪቱን ለስኬት አብቅቷታል የሚሉ ወገኖች ተበራክተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በትኩረት ማነስ ምክንያት ሃገሪቱ እምቅ ችሎታ ባሏቸው ተጫዋቾቿ ሳትጠቀም መቅረቷን ብዙዎች የሚስማሙበት ሃሳብ ነው፡፡
ተስፋ
የጊኒ ቢሳው ተስፋ የተሰጣት ዝቅተኛ ግምት ከጫና ውጪ ሆኗ ጨዋታዎችን ማድረጓ ነው፡፡ በጥንቃቄ መጫወትን ለሚመርጡት ካንዴም ይህ ከጫና ውጪ መሆን ከፍተኛ ጥቅም አለው፡፡ ጊኒ ቢሳውን ከምድቡ የማለፍ ተስፋዋን ዝቅ አድርገው የሚመለከቱ ብዙዎች መሆናቸው ብሄራዊ ቡድኑ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የመጣው በዕድል አለመሆኑን ማስመስከር ይፈልጋል፡፡ የጊኒ ቢሳው ሌላው ጥንካሬ ያገኟቸውን የግብ ማግባት ዕድሎች በአግባቡ የሚጠቀሙ ተጫዋቾችን መያዟ ነው፡፡ ካንዴ የሚከተሉት የጥንቃቄ አጨዋወት ለመከላካል የሚስችላቸው ሲሆን በመልሶ ማጥቃት ቡድኑ ጥሩ እንደሆነ በማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ መመልከት ችለናል፡፡
ስጋት
በጊኒ ቢሳው በኩል ሊነሳ የሚችለው ዋነኛው ስጋት የትልቅ ውድድር ልምድ የሌላቸውን ተጫዋቾች መያዟ ነው፡፡ በ2012 ቦትስዋና ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈችው የመጀመሪያዋ ሃገር ነበረች፡፡ ቢሆንም በማጣሪያው መልካም የነበረው ቡድን ልምድ ስላልነበረው በአፍሪካ ዋንጫው የግብ ናዳ ወርዶበት በግዜ ከምድብ ተሰናብቷል፡፡ ይህ እጣ ፈንታ በጊኒ ቢሳው እንዳይደገም ይሰጋል፡፡ ጊኒ ቢሳው ምንያክል የምትመርጠው የመልሶ ማጥቃት በአፍሪካ ዋንጫ ይጠቅማታል የሚለውም ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡ የሚከተሉት የአምስት ሰው የመሃል ሜዳ እስከየት ያዘልቃቸውል የሚለውም ሌላው ጥያቄ ነው፡፡
የሚጠበቁ ተጫዋቾች
ብዙዎቹ የብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች የሚጫቱት በአውሮፓ በሚገኙ ዝቅተኛ ሊጎች ነው፡፡ ቢሆንም የአማካይ ክፍሉ መሪ ቦካንጂ ካ ከጊኒ ቢሳው ይጠበቃል፡፡ ካ በፈረንሳይ የእግርኳስ ህይወቱን ይመራል፡፡ ጨዋታ የማንበብ እና የመቆጣጠር አቅሙ ጥሩ የሚባል መሆኑ የጊኒ ቢሳው ወሳኝ ተጫዋች እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ወደፊት በመሄዱ የተሻለ የሆነው ዚዚንሆ ነው፡፡ ተጫወቹ በማጣሪያው በተደጋጋሚ ለጊኒ ቢሳው የግብ ማግባት እድሎችን ሲፈጥር እና ሲያስቆጥርም ነበር፡፡ ዚዚንሆ በማጥቃቱ ወረዳ ላይ ስለሚገኝ ለተጋጣሚ ተከላካዮች ራስ ምታት ሊሆን ይችላል፡፡
የማጣሪያ ጉዞ
ጊኒ ቢሳው ከምድብ አምስት ኮንጎ ብራዛቪልን፣ ዛምቢያን እና ኬንያን በልጣ ነው ወደ አፍሪካ ዋንጫው ያለፈችው፡፡ በአምስተኛው ጨዋታ ነበር ጊኒ ቢሳው ዛምቢያ በሜዳዋ 3-2 በማሸነፍ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የሚያሳልፋትን ዕድል ያገኘችው፡፡ ካደረገቻቸው ስድስት ጨዋታዎች ሶስት ስታሸንፍ በአንድ አቻ ወጥታ በሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ሽንፈትን ቀምሳለች፡፡
ሙሉ ስብስብ
ግብ ጠባቂዎች
ጆናስ ሜንዴዝ (ቪሰላ/ፖርቹጋል)፣ ሩይ ዳቦ (ኮቫ ፓይዳድ/ፖርቹጋል)፣ ፓፓ ፎል (አጉአ ዱልስ/ስፔን)
ተከላካዮች
ሄንሪ ኢማኑኤል (ሴሉል/ሮማንያ)፣ ቶማስ ዳቦ (ብራጋ ቢ/ፖርቹጋል)፣ ሩድኒልሰን ሲልቫ (ሊቺያ/ፖላንድ)፣ ኤርዲሰን ሜንዴዝ (ፍራሙንዴ/ፖርቹጋል)፣ ማሪንዮ ጁአሪ( ማፍራ/ፖርቹጋል))፣ አውግስቲንሆ ሱአሬስ(ስፖርት ኮቪላሆ/ፖርቹጋል)፣ ማማዱ ካንዴ (ቶንዴላ/ፖርቹጋል)
አማካዮች
ፍራንሶ ሳንቶስ (ስምስጎድሴት/ኖርዌይ)፣ ላሳና ካማራ (አካዳሚኮ ቪሲ/ፖርቹጋል)፣ ዚዚንሆ (ሌቫዲያኮስ/ግሪክ)፣ ቦካንጂ ካ (ስታደ ሬሚስ/ፈረንሳይ)፣ ናኒሲዮ ሱአሬስ (ፌልጉዌሬዝ/ፖርቹጋል)፣ ቶኒ ሲልቫ (ሌቫዲያኮስ/ግሪክ)፣ ፒኩዊቲ ሲልቫ (ብራጋ ቢ/ፖርቹጋል)፣ ኢድሪሳ ካማራ (ኮሪገስ/ጣሊያን)፣ አልዴር ባልዴ (ሆላነስ/ፖርቹጋል)
አጥቂዎች
አቤል ካማራ (ቤልኔንስ/ፖርቹጋል) ፣ ፍሬድሪክ ሜንዲ(ኦልሰን ሀዩንዳይ/ደቡብ ኮሪያ)፣ ሆልዬ ሳሚ(አኪሳር/ቱርክ)፣ ጃኦ ማሪዮ (ዲ. ቻቬዝ/ፖርቹጋል)
ጊኒ ቢሳው የመጀመሪያ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዋን አዘጋጇን ጋቦንን ቅዳሜ በመግጠም ትጀምራለች፡፡