በ2013 ባልተጠበቀ መልኩ ለፍፃሜ ደርሰው በናይጄሪያ የተሸነፉት ቡርኪናፋሶዎች በ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ከምድብ ማለፍ ተስኗተው በጊዜ ነበር የተሰናበቱት፡፡
አንድ ግዜ ለፍፃሜ ከመቅረቧ ውጪ በአፍሪካ ዋንጫ የገነነ ስም ያላት ቡርኪናፋሶ ከ2010 ወዲህ በአህጉሪቱ ውድድሮች በጠንካራ ተፎካካሪነት ብቅ እያለች ነው፡፡ ቡርኪናፋሶ ወጥ በሆነ አቋም ለተከታታይ አምስት የአፍሪካ ዋንጫዎች ማለፍ የቻለች ሲሆን ከዓመት ዓመት የቡድኑ ተጫዋቾች ከዕድሜ ጋር በተያያዘ እየተተኩ ይገኛሉ፡፡ በ2015 ኤኳቶሪያል ጊኒ ባዘጋጀችው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ያሳዩትን እጅግ የወረደ አቋም ለማሻሻልም ወደ ጋቦን አቅንተዋል፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ብዛት – 11
ውጤት፡ ሁለተኛ (2013)፣ አራተኛ (1998)
አሰልጣኝ፡ ፓውሎ ዱራቴ
ቡርኪናፋሶ በምድብ አንድ ከአዘጋጇ ጋቦን፣ ካሜሮን እና ጊኒ ቢሳው ጋር ተደልድላለች፡፡ ከ2015ቱ የአፍሪካ ዋንጫ የውጤት ቀውስ በኃላ ግርኖት ሮርን ተክተው የቀድሞ የፈረሰኞቹ አሰልጣኝ ፓውሎ ዱራቴ መጥተዋል፡፡
ፓርቹጋላዊው ዱራቴ ለቡርኪናፋሶ እግርኳስ አዲስ አይደሉም፡፡ በ2013 የአፍሪካ ዋንጫ ለፍፃሜ የደረሰው ቡድን ላይ የራሱ የሆነ አሻራ ነበረው፡፡ የያኔው አሰልጣኝ ፓል ፑት ቡድኑን ለተሻለ ደረጃ ቢያደርሱትም የዱራቴ ሚና ግን ላቅ ያለ ነበር፡፡ ትእግስትን የሚፈልገው ቡድኑ በጊዜ ሂደት ፍሬ እንደሚያፈራ እሙን ቢሆንም ከምድብ ለማለፍ ግን በጥንካሬ ለውድድር መግባት አለበት፡፡
ተስፋ
ቡርኪናፋሶ ከ2015ቱ አፍሪካ ዋንጫ በተሻለ ከጫና ነፃ ሆኖ ለውድድር ይቀርባል፡፡ በ2015 ዋንጫውን ለማንሳት ከፍተኛ ግምት የተሰጠው ቡድኑ ባዶ እጁን የምድቡ ግርጌ ሆኖ መመለሱ ጫናን መቋቋም አቅሙ ላይ ጥያቄ እንዲነሳ ያደርጋል፡፡ አሁን ላይ ከዚህ ጫና መላቀቃቸው በተሻለ መንፈስ ወደ ውድድር እንዲገቡ ያደርጋቸዋል፡፡ በጠንካራ አዕምሮ የተገነባው ቡድኑ ወደተፈለገው ውጤት ሊያመራው የሚችል አምበል ይዟል፡፡ አምበሉ ቻርለስ ካቦሬ ከ2010 ጀምሮ በአፍሪካ ዋንጫው የተሳተፈ ሲሆን ቡድኑን የመምራት ብቃቱ የተዋጣለት መሆን ሌላው የቡርኪናፋሶ ተስፋ ነው፡፡ ልምድ ያላቸው እና ፅናት ያላቸውን ተጫዋቾች መያዙ ቡድኑን ከምድብ ቢያንስ ሊያሳልፈው ይችላል፡፡ የተጫዋቾች አዕምሮ ጥንካሬ በምድብ ማጣረያው እንደነበረው የሚቀጥል ከሆነ ቡድኑ ከረጅም ርቀት ሊጓዝ ይችላል፡፡ በፖል ፑት ዘመን ሲተገበር የነበረው የ4-2-3-1 የተጫዋቾች አደራደር ስርዓት ዳግም በዱራቴ ዘመን መተግበር መጀመሩ ለቡርኪናፋሶ መልካም ዜና ነው፡፡
ስጋት
የቡርኪናፋሶ ጨራሽ አጥቂዎች በእድሜ ምክንያት ከቡድኑ መለየት ጀምረዋል፡፡ ቁመተ ለግላጋው አሪስቲዲ ባንሴ በ2013 የነበረው ብቃቱ አብሮት የለም፡፡ ተጫዋቹ የእግርኳስ ህይወቱ ቁልቁል መጓዝ ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ቡድኑ ጥልቀት ይጎለዋል፡፡ በንፅፅር ጨዋታዎች በቶሎ መጨረስ ላይም ቡድኑ ችግሮች አሉበት፡፡ የግብ ማግባት ችግሩም በማጣሪያው ላይ በደንብ ተንፀባርቋል፡፡ ቡድኑ የማጣሪያ ምድቡን በመሪነት ሲያጠናቅቅ ያስቆጠረው ስድስት ግቦች ብቻ ናቸው፡፡ ይህም ለቀድሞ የጋቦን አሰልጣኝ ዱራቴ ትልቅ እራስ ምታት ነው፡፡ ቡድኑ ያለበትን የአጨራረስ ችግር መፍትሄ የማያበጅለት ከሆነ ከምድብ ማለፉ ራሱ ያጠያይቃል፡፡
የሚጠበቁ ተጫዋቾች
ዱራቴ ለሚጠቀሙት የጨዋታ ስልት የተመቹ ተጫዋቾችን ብሄራዊ ቡድኑ ይዟል፡፡ በክለብ ህይወቱ ስኬታማ እያልሆነ የሚገኘው ጆናታን ፔትሮፒያ ለቡርኪናፋሶ ጥሩ ግልጋሎት ሊሰጥ ይችላል፡፡ ፔትሮፒያ ጥሩ የቴክኒክ ብቃት እና ግብ ማስቆጠር ችሎታን አብሮ ያጣመረ ተጫዋቾች ነው፡፡ ወጣቱ ተስፈኛ በርትራንድ ትራኦሬ አሁን ላይ እየበሰለ ነው፡፡ በ2012 የአፍሪካ ዋንጫ በታዳጊነቱ የተጫወተው በርትራንድ በቡርኪናፋሶ መስመር አጨዋወት ላይ ጥሩ ሚናን መውሰድ ይችላል፡፡ በግብፅ ሊግ የሚጫወተው አጥቂው ባኑ ዲያዋራ እድል ከተሰጠው የአጨራረስ ብቃቱ መልካም ነው፡፡ የበርትራንድ ታላቅ ወንድም አሊያን ትራኦሬ ልክእንደ 2013ቱ ሁሉ በጥሩ ብቃት ላይ ከተገኘ ቡድኑን በሰፊው ሊረዳ ይችላል፡፡
የማጣሪያ ጉዞ
ቡርኪናፋሶ በምድብ አራት ከዩጋንዳ፣ ቦትስዋና እና ኮሞሮስ ጋር ነበር የተመደበችው፡፡ በመክፈቻው ጨዋታ ከቦትስዋና ላይ ነጥብን በመውሰድ የጀመረችው ቡርኪናፋሶ ዩጋንዳን በተከታታይ ነጥብ ማስጣሏ ምድቡን በመሪነት እንድትጨረስ አስችሏታል፡፡ በተለይ ብዙ ሃገራት ከሚቸገሩበት ካምፓላ ላይ አንድ ነጥብ ይዛ መመለሷ የተሳካ የማጣሪያ ውድድር እንድታሳልፍ አስችሏታል፡፡ ቡርኪናፋሶ ካደረገቻቸው ስድስት ጨዋታዎች በአንድ ስትሸነፍ በአራቱ አሸንፋ በአንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርታለች፡፡
ሙሉ ስብስብ
ግብ ጠባቂዎች
አቡበከር ሳዋዶጎ (ሬይል ክለብ ዱ ካዲዮጎ/ቡርኪናፋሶ)፣ ሄርቬ ኮፊ (አሴክ አቢጃን/ኮትዲቯር)፣ ጀርሜን ሳኖ (ቢዮቬስ/ፈረንሳይ)
ተከላካዮች
ስቲቭ ያጎ (ቱሉዝ/ፈረንሳይ)፣ ኢሶፍ ፓሮ(ሳንቶስ/ደቡብ አፍሪካ፣ ባካሪ ኮኔ (ማላጋ/ስፔን)፣ ፓትሪክ ማሎ (ሰሞሃ/ግብፅ)፣ ሱሌማና ኮአንዳ (አሴክ አቢጃን/ኮትዲቯር)፣ ኢሶፎ ዳዮ (ሬሲንግ ክለብ ደ በርካን/ሞሮኮ)፣ ያኮባ ኩሊባሊ (አርሲቢ/ቡርኪናፋሶ)
አማካዮች
ባካሪ ሳሬ (ሞሪሬንስ/ፖርቹጋል)፣ ፕሪጁስ ናኮልማ (ካይሰርስፖር/ቱርክ)፣ አብዱልራዛክ ትራኦሬ (ካራቡክስፖር/ቱርክ)፣ አሊያን ትራኦሬ (ካይሰርስፖር/ቱርክ)፣ ጆናታን ፔትሮፒያ (አል ናስር/የተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች)፣ አዳማ ጉይራ (ሬሲንግ ክለብ ደ ሌንስ/ፈረንሳይ)፣ ቻርለስ ካቦሬ (ክራስኖዳር/ሩሲያ)፣ በርትራንድ ትራኦሬ(አያክስ አምስተርዳም/ኔዘርላንድ)፣ ባሬስ ሲሪል (ሸሪፍ ቲራስፖል/ሞልዶቫ)፣ ብላቲ ቱሬ (ኦሞኒያ ኒኮዢያ/ቆጵሮስ)
አጥቂዎች
አሪስቲዲ ባንሴ (አሴክ አቢጃን/ኮትዲቯር)፣ ባኑ ዲያዋራ (ሰሞሃ/ግብፅ)፣ ጆናታን ዞንጎ (አልሜሪያ/ስፔን)
ቡርኪናፋሶ የምድብ መክፈቻ ጨዋታዋን ካሜሮንን ቅዳሜ በመግጠም ትጀምራለች፡፡