በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት መርሃግብር ደደቢት እና መከላከያን ያገናኘው ጨዋታ ያለግብ በአቻ ውጤ ተጠናቋል፡፡
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እጅግ የተቀዛቀዘ እና የሚጠቀሱ የግብ ሙከራዎች ያልታየበት ነበር፡፡
በመጀመሪያው አጋማሽ ደደቢቶች ይዘው በገቡት የ3-5-2 የጨዋታ ቅርፅ የነበራቸውን የመሀል ሜዳ የቁጥር ብልጫ መጠቀም አልቻሉም፡፡ በአንጻሩ በዝርግ 4-4-2 ወደ ጨዋታው የገቡት መከላከያዎች በራሳቸው የሜዳ አጋማሽ ኳሶችን በመቆጣጠር በተደጋጋሚ በረጅሙ ፊት ላይ ለሚገኙት ፈጣን አጥቂዎቻቸው ለማድረስ ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡ ነገርግን በመጀመሪያው አጋማሽ እንደነበራቸው አንጻራዊ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ይህ ነው የሚባል የግብ እድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ታይቷል፡፡ በተቃራኒው ከቋሙ ኳሶች በሚሻሙ ኳሶች ጥቂት የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፡፡
በጨዋታው ላይ የመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ የተስተናገደው በ22ኛው ደቂቃ ላይ ነበር፡፡ ምንይሉ ወንድሙ ከደደቢት የግብ ክልል ውጪ የተገኘችውን ኳስ አክርሮ በመምታት ቢሞክርም ክሊመንት አዞንቶ አድኖበታል፡፡ በድጋሚ በ26ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ሳሊሶ ያሻማውን የማእዘን ምት ምንይሉ ቢገጭም አሁንም ክሊመንት የሚቀመስ አልሆነም፡፡ በተመሳሳይ በ44ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳሊሶ ያሻማውን የማእዘን ምት አወል አብደላ ገጭቶ ቢሞክርም ክሊመንት ሊያድንበት ችሏል፡፡
ደደቢቶች በመጀመሪያው አጋማሽ ጌታነህ ከበደ ከቅጣት ምት ሞክሮ ወደ ውጪ ከወጣበት ኳስ በስተቀር ወደ ተቃራኒ የሜዳ ክልል በመግባት የግብ እድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ታይተዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ከመጀመሪያው አጋማሽ እጅጉን ተቀዛቅዘው ታይተዋል፡፡ በዚህም መሀል ሜዳ ላይ በነበሩ ሹክቻዎች እና ቶሎ ቶሎ ኳስ መነጣጠቆች በብዛት የተስተዋሉበት ነበር፡፡ በዚህ አሰልቺ በነበረው የሁለተኛው አጋማሽ ይህ ነው የሚባል ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራም አልተስተናገደበትም፡፡
በ82ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያው ተከላካይ ሽመልስ ተገኝ ኳስ ወደ ውጭ ለማውጣት ሲል የመታት ኳስ በአቅራቢያው የነበረውን የደደቢቱን አምበል ብርሃኑ ቦጋለን ጭንቅላት በመምታቱ ብርሃኑ ምላሱን ውጦ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ራሱን ስቶ ነበር፡፡ ነገርግን በራሱ በሽመልስ ተገኝ እንዲሁም በተደረገለት የህክምና ርብርብ ህይወቱ ልትተርፍ ችላለች፡፡ ለበለጠ ህክምናም በቀጥታ ወደ ቤተዛታ ሆስፒታል ተወስዷል፡፡
በጨዋታው መገባደጃ አካባቢ ደደቢቶች መጠነኛ ብልጫ በመውሰድ የግብ እድሎች ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ በ89ኛው ደቂቃ ላይ ስዩም ከማእዘን ያሻማውና አክሊሉ አያናው ሞክሮ አቤል ማሞ ያዳነበት ኳስ ተጠቃሽ ነበረች፡፡