አዲሱ የሼክ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታድየም የመጀመርያ የሆነውን የነጥብ ጨዋታ ባስተናገደበት ጨዋታ ወልድያ እና ድሬደዋ ከተማ ያለግብ በአቻ ውጤት አጠናቀዋል፡፡
ስታድየሙ የመጀመርያ ጨዋታ እንደማስተናገዱ መጠን በርካታ ቁጥር ባለው ተመልካች ይሞላል ተብሎ ቢጠበቅም ከተጠበቀው በታች ተመልካች በስታድየም ተገኝቷል፡፡ ነገር ግን ጨዋታው ከተጀመረ በኋላ ተመልካቹ በነጻ እንዲገባ በመፈቀዱ ቁጥሩ በርከት ያለ ተመልካች ወደ ሜዳ ሊገባ ችሏል ።
ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ ዳሽን ቢራ ፋብሪካ ለወልድያ ስፖርት ክለብ በ5 አመታት ተከፋፍሎ ገቢ የሚደረግ 25 ሚልዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡ የእለቱ የክብር እንግዶች የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር አረጋ ይርዳው ተጨዋቾችን በመተዋወቅም ነበር ጨዋታው የተጀመረው፡፡
በመጀመርያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል ማራኪና ሳቢ የሆነ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታደ ሲሆን የጎል ሙከራ በማድረግ በኩል እንግዶቹ ድሬዳዋዎች ቀዳሚ ነበሩ፡፡ 4ኛው ደቂቃ ላይ ዘነበ ከበደ መቶት ቤሊንጌ ሲተፋው በቅርብ ርቀት የነበረው ሀብታሙ ወልዴ ሞክሮ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ድሬዳዋን መሪ ሊያደርግ የሚችል መልካም አጋጣሚ ነበር፡፡
ከዚህ ሙከራ በኃላ ባለ ሜዳዎቹ ወልድያዎች የተሻለ እንቅስቃሴ በማሳየት በ11ኛው ደቂቃ ቢንያም ዳርሰማ ፤ በመጀመርያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ደቂቃ ደግሞ አንዱአለም ንጉሴ መልካም የጎል አጋጣሚ ቢፈጥሩም ሳይጠቀሙበት የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡
ከእረፍት መልስ ጨዋታው በተጀመረ ቅፅበት አንዱአለም ንጉሴ ከግብ ጠባቂው ሳምሶን ጥላሁን ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ አስቆጠረ ሲባል ያመከነው ኳስ የማይታመን ነበር።
ጨዋታው በጥሩ ግለትና በፈጣን እቅንቅስቃሴ ሞቅ ብሎ እየቀጠለ ባለበት አጋጣሚ 60ኛው ደቂቃ ላይ የወልድያው አማካይ ዳንኤል ደምሴ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል፡፡
ከቀይ ካርዱ በኋላ የተጨዋቾች የቁጥር ማነስን ተከትሎ ወልድያዎች ጎላቸውን ላለማስደፈር መከላከልን ምርጫቸው አድርገዋል፡፡ ድሬደዋ ከተማ የቁጥር የበላይነቱን ተጠቅሞ ለማሸነፍ የተጨዋች ለውጥ በማድረግ የአጥቂ ቁጥሩን ቢያበዛም ደካማው የድሬደዋ የአጥቂ መስመር ተጨዋቾች ይህ ነው የሚባል ጠንካራ የጎል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም፡፡ በአንፃሩ ወልድያዎች በመልሶ ማጥቃት ጫና ለመፍጠር ቢሞክሩም ጎል ሳይቆጠር ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል ።