የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ 80ኛ ዓመት ክብረ በአል አርማ በይፋ ተመረቀ

ቅዱስ ጊዮርጊስ በቅሎቤት በሚገኘው የክለቡ ፅህፈት ቤት ዛሬ በተደረገ ስነ ስርዓት ክለቡ የቦርድ ሊቀመንበር እና ፕሬዝዳንት አቶ አብነት ገብረመስቀል በተገኙበት አርማውን በይፋ አስመርቋል።

የክለቡ የሲምፖዚየም እና መፅሄት ዝግጅት ኮሚቴ ባወጣው የአርማ ውድድር ላይ 13 ግራፊክስ ዲዛይነሮች የተሳተፉ ሲሆን አቶ ቴዎድሮስ ግደይ የተባሉ ተወዳዳሪ ውድድሩን በማሸነፍ የ10ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነዋል። የክለቡ ደጋፊ የሆነችው ነፃነት ሬጋን ውድድሩን በሁለተኛ ደረጃ በመጨረስ የ7500 ብር ተሸላሚ ሆናለች።

DSC00222

 

ስለ አርማው የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ልዑልሰገድ በርታ “በምንፈልገው አይነት ዲዛይን ተሰርቶ ቀርቦልናል፤ ጥሩ አርማ አዘጋጅተናል ብዬ አስባለሁ” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የክለቡ ቦርድ ሊቀመንበር እና ፕሬዝዳንት አቶ አብነት ገብረመስቀል በበኩላቸው “ከፍተኛ ጥረት ተደርጎ አርማው ተሰርቷል። ጊዮርጊስ ታሪካዊ ክለብ ነው፤ የኢትዮጵያም ታላቁ ክለብ ነው። የ80ኛ አመት ክብረ በአል በሚገልፅ መልኩ አርማው በመሰራቱ ደስተኛ ነኝ። ምልክቱ ‘V’ ደግሞ ደም የፈሰሰበት ነው።” በማለት ተናግረዋል።

2nd winner
በውድድሩ ሁለተኛ ደረጃን ያገኘው አርማ

 

ዛሬ የተመረቀው አርማ ለክለቡ 80ኛ ዓመት ልደት ማድመቂያ የሚውል እንጂ ክለቡ አሁን የሚጠቀምበትን አርማ እንደማይለውጥ ተነግሯል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ በታህሳስ ወር 1928 ዓ.ም. የተመሰረተ ሲሆን በቀጣዩ ዓመት ታህሳስ ወር 2008 80ኛ ዓመቱን ይይዛል። ሚያዝያ 10፣ 2007 በሚሊንየም አዳራሽ በሚኖረው የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ የክለቡ 80ኛ ዓመት ክብረ በአል በይፋ እንደሚጀመር ታውቋል። ክብረ በአሉ በተለያዩ ዝግጅቶች እስከ ታህሳስ 2008 ድረስ እንደሚቀጥል ክለቡ አስታውቋል።

በተያያዘ ዜና የቅዱስ ጊዮርጊስ ከ17 ዓመት በታች ቡድን በ2006 ዓ.ም. ላመጣው ውጤት ክለቡ ሽልማት ሰጥቷል። ሽልማቱን የክለቡ የቦርድ አመራሮች አቶ አብነት ገብረመስቀል፣ አቶ ታፈሰ በቀለ እና አቶ ኢሳያስ ዓለሙ ለተጫዋቾቹ ሰጥተዋል።

Abubeker Sani

የክለቡ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብነት ገብረመስቀል በሽልማት ስነ ስርዓቱ ላይ “ወጣቶቹ ባመጡት ውጤት ደስተኛ ነኝ። ጊዮርጊስ ቀላል ቡድን አይደለም፤ የእናንተ ትከሻ የሚለካው በሴንቲ ሜትር ሳይሆን ሃላፊነትን በመሸከም በምታመጡት ውጤት ነው። የአቡበከር ሳኒን ፈለግ ተከትላችሁ እናንተም ወደ ዋናው ቡድን እንድታድጉ ጠንክራችሁ መስራት ይኖርባችኋል።” ሲሉ መልዕክታቸውን ለተጫዋቾቹ አስተላልፈዋል። አምና ከ17 ዓመት ቡድኑን በአምበልነት ሲመራ የነበረው አቡበከር ሳኒ ወደ ዋናው ቡድን አድጎ በመጫወት ላይ መሆኑ ይታወቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *