በመጀመርያው የማጣርያ ጨዋታ በደቡብ አፍሪካ አቻው በገዛ ሜዳው 2-0 የተሸነፈው የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ነገ የመልስ ጨዋታውን ከሜዳው ውጪ ያደርጋል፡፡
በአሰልጣኝ ወንድማገኝ ከበደ የመሚመራው ብሄራዊ ቡድን ትላንት ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀና ሲሆን የዋናው ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ አብረው ተጉዘዋል፡፡ አሰልጣኝ ባሬቶ ወደ ሀገር ቤት ከተመለሱ ወዲህ ከ20 አመት በታች ቡድኑን ሲያዘጋጁና መሰረታዊ የመከላከል እና የማጥቃት ልምምዶችን ሲያሰሩ እንደሰነበቱ አሰልጣኝ ወንድማገኝ የገለፁ ሲሆን ተጫዋቾቹ ለኢንተርናሽናል ውድድሮች አዲስ በመሆናቸውና ለማሸነፍ በነበራቸው ጉጉት ምክንያት በአእምሮ ረገድ መረጋጋት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን በደቡብ አፍሪካ መሸነፉን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በፕሪሚየር ሊጉ እና ብሄራዊ ቡድን የመጫወት ልምድ ያላቸውን ሳላዲን በርጊቾ ፣ ቶክ ጄምስ እና ጋቶች ፓኖምን ለማካተት የወሰነ ቢሆንም የካፍ የተጫዋቾች ማስመዝገብያ ቀነ ገደብ በማለፉ ተጫዋቾቾቹ ሳይካተቱ ቀርተዋል፡፡
17 ተጫዋቾችን የያዘው ብሄራዊ ቡድኑ ጆሃንስበርግ ሲደርስ በአየር ማረፍያው የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ እና 3 ተጫዋቾች ከወረቀት ስራዎች ጋር በተያያዘ መጉላላት የደረሰባቸው ሲሆን በትላንቱ ልምምድ ላይም መገኘት አልቻሉም፡፡ ሶስቱ ተጫዋቾች ዘግይተው ቡድኑን የተቀላቀሉ ሲሆን ዛሬ ከሰአት በሚጫወቱበት ስታድየም በሚያደርጉት ልምምድ ላይ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ነገ በ10 ሰአት በጆሃንስበርግ የሚደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 በቀጥታ ይተላለፋል፡፡{jcomments on}