የቢንያም በላይ የዳይናሞ ድረስደን ሙከራ አልተሳካም

በቡንደስሊጋ 2 የሚወዳደረውና የምስራቅ ጀርመን ድረስደን ከተማ ክለብ የሆነው ኤስጂ ዳይናሞ ድረስደን ለኢትዮጵያዊ አማካይ ቢኒያም በላይ የሁለት ሳምንት የሙከራ ግዜ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ክለቡ በቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅት ላይ ቢኒያምን በሶስት ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ሁለት ግቦችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል፡፡ እንደ ጀርመኑ ድረ-ገፅ tag24.de ዘገባ ከሆነ ዳይናሞ ድረስደን እንደተጠበቀው ውል ከመስጠት ታቅቧል፡፡ ክለቡ ቢኒያምን ለማስፈረም ፍላጎት እንደሌለውም tag24.de ዘግቧል፡፡

ቢኒያም በሁለት ሳምንት የድረስደን ቆይታው ሃንተርሃቺንግ እና ቪክቶሪያ በርሊን ላይ ግቦችን አስቆጥሯል፡፡ የድረስደን ዋና አሰልጣኝ ኡዊ ኔሁስ በተለይ ቅዳሜ ከተደረገው ሃንተርሃቺንግ ጨዋታ በኃላ ስለቢኒያም ቀጣይ ቆይታ እንደሚወስኑ መናገራቸው ዘግቧል፡፡ ኔሁስ ስለቢኒያም “የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ አልነበረም ምንም እንኳን የመንቀሳቀስ ፍላጎት ቢያሳይም፡፡ ቢሆንም ቢኒያም ሜዳ ላይ ይበልጥ ነፃ ነበር፡፡ ወደ ድረስደን ስንመለስ ስለቀጣይ ሁኔታ እናስብበታለን ሲሉ” ነበር የተናገሩት፡፡

ዳይናሞ ድረስደን እሁድ እለት እንደተገለፀው ቢኒያምን አያስፈርምም፡፡ የታክቲክ አረዳድ ላይ ቢኒያም ያለው ድክመት እና በመከላከል ላይ ያለው ተመናመነ ሚና ዳይናሞ ድረስደን አማካዩን እንዳያስፈርም እንዳደረገው የሚወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ ዳይናሞ ድረስደን በሚቀጥለው አመት ወደ ቡንደስሊጋ 1 ለማደግ የሚያደርገው ጥረት የሚያስፈርማቸው ተጫዋቾች በቶሎ ሊጉን እንዲላመዱ መፈለጉም እንደምክንያት ተጠቅሷል፡፡ በታክቲክ አረዳድ ላይ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች በቂውን ክትትል እና ስልጠና አለማግኘታቸው በሙከራ ግዜ እንዲቸገሩ እንደሚያደርጋቸው በሰፊው ይታመናል፡፡

ቢኒያም እስከ ነሃሴ 2 የሚቆይ ቪዛ ስላለው በሌሎች ክለቦች ሙከራውን እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡

ተጫዋቹ ወደ ጀርመን እንዲያመራ ሁኔታውን ያመቻቹት ጀርመናዊው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ቴክኒክ አማካሪ ዩአኪም ፊከርት ከሁለት ሳምንት በፊት ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት በሌሎች ክለቦች ቢኒያም የሙከራ እድልን እንደሚገኝ መጥቀሳቸው ይታወሳል፡፡ ቢኒያም አምና በተመሳሳይ በቦሩሺያ ሞንቼግላድባህ ተስፋ ሰጪ ሙከራ ማድረጉ ይታወቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *