ጌታነህ ከበደ ከዊትስ ጋር ተለያየ

ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ጌታነህ ከበደ ከደቡብ አፍሪካው ክለብ ቤድቬስት ዊትስ ጋር መለያየቱ ታውቋል፡፡ ያላፈውን የውድድር ዘመን በተቀማጭ ወንበር ላይ ያሳለፈው የቀድሞ የደቡብ ፓሊስ እና ደደቢት አጥቂ ከዊትስ ጋር እንደሚለያይ ቀደም ብሎ ይታወቀ ነበር፡፡ ዊትስ ጌታነህን በውሰት ለሌላ ክለብ ለመስጠት ወይም ለመሸጥ እንደሚፈልግ ከዚህ በፊት መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡ የአንድ ዓመት ቀሪ ውል የነበረው ጌታነህ ከዊትስ ጋር በስምምነት ተለያይቷል፡፡ በ2013 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ስኬት ተከትሎ ወደ ዊትስ ያመራው ጌታነህ ቀጣይ ማረፊያ ደቡብ አፍሪካው ክለብ ዩንቨርሲቲ ኦፍ ፕሪቶሪያ ሊሆን እንደሚችል ተዘግቧል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን የሰጡን የኤስኤቢሲ የእግርኳስ ጋዜጠኛ ደቡብ አፍሪካዊው ቪሊል መቡሊ “ጌታነህን እና ዊትስ በስምምነት ተለያይተዋል፡፡ አማ ተክስ (ዩንቨርሲቲ ኦፍ ፕሪቶሪያ) የልጁ ፈላጊ ክለብ ነው፡፡ ስለዚህም ጌታነህ በደቡብ አፍሪካ ሊቆይ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡”

አያክስ ኬፕ ታውን የጌታነህ ፈላጊ ሌላ ክለብ ነው ለሚሉት ዘገባዎች መቡሊ “አይመስለኝም! አያክስ ኬፕ ታውን ጥሩ ደሞዝ አይከፍልም፡፡ ለጌታነህም ምንም አይነት የዝውውር ጥያቄ ያቀረቡ አይመስለኝም፡፡” ብለዋል፡፡

የጌታነህ መልቀቅ ኬንያዊውን የቀድሞ ኤፍሲ ሊዮፓርድስ፣ ሶፋፓካ፣ ተስካር እና አል-ሜሪክ አጥቂ አለን ዋንጋ ወደ ዊትስ እንዲያመራ የሚያስችለው ይሆናል፡፡