ሰንዳፋ በኬ እና ጉለሌ ለክልል ክለቦች ሻምፒዮና ፍፃሜ ደርሰዋል

የክልል ክለቦች ሻምፒዮና የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች እሁድ ተደርገው ሰንዳፋ በኬ እና ጉለሌ ክፍለከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፈዋል፡፡

ሰንዳፋ በኬ 2-2 (4-2) ናኖ ሁርቡ

በ8:00 ናኖ ሁሩቡ ከ ሰንዳፋ በኬ ተገናኘተው ሰንዳፋ በመለያ ምቶች አሸንፏል። ያሬድ አለማየሁ በ5ኛው ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ በማራኪ ሁኔታ በሰንዳፋ በኬ መረብ ላይ ያስቆጠረው ግብ ገና ከጅምሩ ናኖዎችን ቀዳሚ አድርጓል። ሰንዳፋ በኬዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ተጭነው በመጫወት በርካታ የግብ አጋጣሚዎች መፍጠር ቢችሉም በአጨራረስ ችግር ምክንያት ግብ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል። ባገኙት አጋጣሚዎች አደጋ ሲፈጥሩ የነበሩት ናኖዎች በ40ኛው ደቂቃ በኤርሚያስ ጥበበ አማካኘነት አስቆጥረው በ2-0 መሪነት ወደ እረፈት አመሩ ተብሎ የዳኛ ፊሽካ ሲጠበቅ ከድር ናስር ባስቆጠረው የቅጣት ምት ግብ 2-1 በሆነ ውጤት ወደ እረፍት አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴ የተስተዋለ ሲሆን የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ፍላጎት ሲስተዋልባቸው የነበሩት ሰንዳፋዎች በ64ኛው ደቂቃ ዮሀንስ ጌታቸው ባስቆጠረው ግብ አቻ ሆነዋል። ከዚህ በኋላ አላስፈላጊ መጎሻሸሞች እና እልህ መጋባቶች የተስተዋሉ ሲሆን በ2-2 ውጤትም መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቋል፡፡

ሁለቱም የግብ ጠባቂ ለውጥ አድርገው በጀመሩት ወደ መለያ ምት ሰንዳፋ በኬዎች 4-2 አሸንፈዋል፡፡ የሰንዳፋ ግብ ጠባቂ ፍቅረ ማሪያም ድሪባም ከተመቱበት ምቶች 2 በማዳን ለሰንዳፋ በኬ ድል ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።

ጉለሌ 1-0 አቃቂ ቃሊቲ

ቀጥሎ በተካሄደው ጨዋታ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የተስተዋለበት ሲሆን ሁለቱም ከቆሙ ኳሶች ሁለቱም አደጋ ሲፈጥሩ ተስተውሏል።
በ15ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የሞከሩትን ኳስ አቃቂዎች በአግባቡ ከግብ ክልላቸው ማራቅ ባለመቻላቸው በረከት አምባዬ አስቆጥሮ ጉለሌን ቀዳሚ አድርጓል። በዚህም ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ ጫና ፈጥረው የተጫወቱት አቃቂዎች የጉለሌ የተከላካይ መስመር አልፎ ግልፅ የሆነ የግብ አጋጣሚ ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። ጉለሌዎች በአንፃሩ በመልሶ ማጥቃት ፈጥረውት የነበውን አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም ቢችሉ ኖሮ መሪነታቸው ከዚህም በሰፋ ነበር።
ጨዋታው በጉለሌ 1-0 አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ አሳፋሪ እና ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ የሆነ ድብድብ በሁለቱ ቡድኖች መካከል የተፈጠረ ሲሆን ጠቡን ለማቆም የፖሊስ ጣልቃ ገብነት አስፈልጎም ነበር፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *