ጋና 2018፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ተጋጣሚዋን አውቃለች

ጋና በ2018 የምታስተናገደው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ላይ የሚሳፉ ሰባት ሃገራትን ለመለየት የሚደረጉ የማጣሪያ ጨዋታዎች በየካቲት ወር ይደረጋሉ፡፡ ኢትዮጵያም በመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ሊቢያን በመግጠም የማጣሪያ ጉዞዋን ትጀምራለች፡፡

በ2012 ኤኳቶሪያል ጊኒ ካስተናገደችው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ከተሳተፉ በኃላ ከአህጉሪቱ ውድድር የራቁት ሉሲዎቹ ለ2018ቱ ውድድር ለማለፍ ሊቢያን ከሜዳዋ ውጪ በመግጠም ትጀምራለች፡፡ ኢትዮጵያ እና ሊቢያ የሚያደርጉት የደርሶ መልስ ጨዋታ ከየካቲት 19 – የካቲት 27 ባሉት ቀናት የሚደረግ ይሆናል፡፡ ሉሊዎቹ ሊቢያን መርታት ከቻሉ በሁለተኛው እና የመጨረሻው ዙር ማጣሪያ የሴኔጋል እና አልጄሪያን አሸናፊ የሚገጥሙ ይሆናል፡፡ በሊቢያ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋትን ተከተሎ የሃገሪቱ ብሔራዊ ቡድን እና ክለቦች ጨዋታቸውን በመረጡት የገለልተኛ ሜዳ በተለይ ቱኒዚያ፣ ግብፅ እና አልጄሪያ ላይ ሲደረግ የቆየ ሲሆን የሊቢያ እና የኢትዮጵያም የመጀመሪያ ጨዋታ የሊቢያ እግርኳስ ፌድሬሽን በሚመርጠው ሜዳ የሚካሄድ ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያ በ2014 ናሚቢያ ካስተናገደችው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ በጋና ተሸንፋ ከውድድር ስትወጣ ካሜሩን በ2016 ካስተናገደችው ውድድር ደግሞ በአልጄሪያ በአጠቃላይ ውጤት 2-1 ተሸንፋ ወደ የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ሳታልፍ ቀርታለች፡፡ ኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በአሰልጣኝ መሰረት ማኔ መሪነት ዩጋንዳ ከአንድ ዓመት በፊት ያስተናገደችውን የሴካፋ ሴቶች ቻምፒየንሺፕ ላይ ከተሳተፈ በኃላ ከጨዋታ ርቋል፡፡

የወቅቱ የአፍሪካ ቻምፒዮና ናይጄሪያ፣ ካሜሮን፣ ኤኳቶሪያል ጊኒ እና ደቡብ አፍሪካ ወደ መጨረሻው የማጣሪያ ዙር በቀጥታ ያለፉ ሃገራት ናቸው፡፡

የማጣሪያ ድልድሉ ይህንን ይመስላል፡፡
አንደኛ ዙር የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ከየካቲት 19 – የካቲት 27/ 2010 (ካፍ በቀጣይ ጨዋታዎቹ የሚደረጉበትን ቀናት ይፋ ያደርጋል)
ሴኔጋል ከ አልጄሪያ
ሊቢያ ከ ኢትዮጵያ
ሞሮኮ ከ ኮትዲቯር
ሴራ ሊዮን ከ ማሊ
ቡርኪና ፋሶ ከ ጋምቢያ
ኮንጎ ከ የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ
ኬንያ ከ ዩጋንዳ
ሌሶቶ ከ ስዋዚላንድ
ታንዛኒያ ከ ዛምቢያ
ናሚቢያ ከ ዚምባቡዌ

የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ከመጋቢት 24 – ሚያዚያ 2/ 2010 ባሉት ቀናት
የሴኔጋል እና አልጄሪያ አሸናፊ ከ የሊቢያ እና ኢትዮጵያ አሸናፊ
የሞሮኮ ከ ኮትዲቯር አሸናፊ ከ የሴራ ሊዮን እና ማሊ አሸናፊ
የቡርኪና ፋሶ እና ጋምቢያ አሸናፊ ከ ናይጄሪያ
የኮንጎ እና የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ አሸናፊ ከ ካሜሮን
የኬንያ እና ዩጋንዳ አሸናፊ ከ ኤኳቶሪል ጊኒ
የሌሶቶ እና ስዋዚላንድ አሸናፊ ከ ደቡብ አፍሪካ
የታንዛኒያ እና ዛምቢያ አሸናፊ ከ የናሚቢያ እና የዚምባቡዌ አሸናፊ