​የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ዝግጅት – ባህርዳር ከተማ

የ2010 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ጥቅምት 24 ይጀመራል፡፡ በሁለት ምድብ በተከፈለው ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማደግ ከፍተኛ ፉክክር ሲጠበቅ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ካደረጉ ክለቦች መካከል ባህርዳር ከተማ ይጠቀሳል፡፡ 

ባለፉት አመታት ባህርዳር ከተማ በከፍተኛ ሊጉ ያሉበትን ድክመቶች በሚገባ መፈተሹን ያስታወቀ ሲሆን በተለይ የተጫዋቾች በፍጥነት መልምሎ ያለማስፈረም፣ በተጨዋቾች ዝውውር ላይ ሙሉ ለሙሉ አሰልጣኙ ተጨዋቾችን እንዲመርጥ እድል አለመስጠት፣ የአሰለጣጠን መንገድ፣ ጠንካራ የቡድን መንፈስ አለመኖር፣ የደጋፊውን አድቫነቴጅ ባለመጠቀም በሜዳው የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች አብዛኛውን በአቻ ውጤት ማጠናቀቅ  እና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ክፍተቶች በቡድኑ ውጤት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ማድረጉ ሲገለፅ ከነዚህ ችግሮች በመነሳት በ2010 የውድድር ዘመን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የክለቡን አወቃቀር እና የአደረጃጀት ላይ ለውጥ በማድረግ ከፍተኛ ስራ መሰራቱ ተገልጿል።

ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ከአሰልጣኝ ቅጥር  ጀምሮ በርካታ ስራዎች እንደተሰሩ ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያሳያል። ባህርዳር ከነማን በዋና አሰልጣኝነት  ኢትዮዽያ ቡናን በተጨዋችነት እና ባሰልጣኝነት ያገለገለው አምና ከሀዲያ ሆሳህና ጋር እስከ መጨረሻው የመለያ ጨዋታ ድረስ ሲያሰለጥኑ የቆዩት አሰልጣኝ ዻውሎስ ጌታቸው የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አድረጎ ሲሾም በምክትል አሰልጣኝነት የቀድሞ የአርባምንጭ ጨርቃ ድንቅ ተጫዋች መኮንን ገላነህ ተሹመዋል ።

ከመስከረም ወር መጀመርያ አንስቶ በባህርዳር ከተማ ላይ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እያደረገ የሚገኘው ባህርዳር ከተማ አምና ከነበረው ስብስቡ ስምንት ተጨዋቾችን በማስቀረት ወደ ቡድኑ በርከት ያሉ ተጨዋቾችን በመቀላቀል አዲስ ቡድን እየገነባ ይገኛል። ኃይማኖት አዲሱ (ግብጠባቂ/ሱሉልታ ከተማ) ፣ ምንተስኖት አድጎ (ግብጠባቂ /ፋሲል ከተማ)፣ ሰለሞን ብሩ (ጅማ አባ ጅፋር)፣ ዮናስ ደስታ (ለገጣፎ)፣ ወንድሜነህ ደረጄ ( ሱሉልታ)፣ ፍቅረሚካኤል አለሙ (ፋሲል ከተማ)፣ ኪሩቤል ተካ ( ጅማ አባቡና)፣ ሳለአምላክ ተገኝ (ኢትዮዽያ ቡና)፣ እንዳለ ከበደ (ወልዋሎ)፣ ሙሉቀን ታሪኩ (ፋሲል ከተማ)፣ ያለው ፋንታሁን (ሀዲያ ሆሳህና)፣ ደረጄ መንግስቱ (ንግድ ባንክ)፣ ሐብታሙ ንጉሴ (አውስኮድ) አዲስ ፈራሚዎች ሲሆኑ የድሬዳዋ ከተማው አጥቂ ፍቃዱ ወርቁ በቅርብ ቀን ቡድኑን የተቀላቀለው ሌላው አዲስ ፈራሚ ነው።

አሰልጣኝ ዻውሎስ ጌታቸው በቅድመ ዝግጅት ልምምድ ወቅት ቡድኑን ለውድድር ለማብቃት ከፍተኛ የቅንጅት ስራ እያሰሩ መሆኑን የተመለከትን ሲሆን ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማስገባት ካለው ልምድ በመነሳት የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ባህርዳር ከነማ ጥቅምት ሃያ አምስት በሚጀመርረው የከፍተኛ ሊግ የውድድር መርሐግብር መሰረት የመጀመርያውን ጨዋታ ሜዳው ላይ አክሱም ከተማን የሚገጥም ይሆናል።

በከፍተኛ ሊጉ ከሚገኙ ክለቦች መካከል በክረምቱ ባደረጉት እንቅስቃሴ እና ያለፈው አመት ባስመዘገቡት ውጤት መሰረት ዘንድሮ ጠንካራ ተፎካካሪ ሊሆኑ የሚችሉ ሌሎች ክለቦችን ዝግጅት በቀጣይ ይዘን እንመለሳለን፡፡