​የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በፎርፌ ወደ ቀጣዩ የማጣርያ ዙር አልፏል

የኢትየጵያ ሴቶች ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን በ2018 በዩራጓይ አስተናጋጅነት በሚከናወነው ከ17 አመት በታች የሴቶች የአለም ዋንጫ ለመሳተፍ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ከኬንያ ጋር ለማድረግ ቢመደብም ኬንያ ከውድድሩ ራሷን በማግለሏ ታዳጊዎቹ ሉሲዎች ወደ ቀጣዩ የማጣርያ ዙር በፎርፌ አልፈዋል፡፡

በአሰልጣኝ ሰላማዊት ዘርአይ የሚሰለጥነው ቡድኑ 36 ተጨዋቾችን በመጥራት በወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ ሜዳ በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላለበት የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታ ልምምድ ማድረግ መጀመሩ የሚታወቅ ሲሆን ተጋጣሚው ኬንያ ጨዋታውን እንደማያደርግ መገለፁን ተከትሎ የመጀመርያ የነጥብ ጨዋታውን ለማድረግ እስከ ህዳር ወር አጋማሽ ድረስ ለመጠበቅ ይገደዳል፡፡

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ዋና ፀሃፊ የሆኑት ወንድምኩን አላዩ የኬንያን ከማጣሪያው ውጪ መሆን ለሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጠዋል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ ከኬንያ እግርኳስ ፌድሬሽን ቅርበት ካላቸው ምንጮች እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ የኬንያ ተማሪዎች እስከ ህዳር 7 ድረስ በፈተና ላይ መገኘታቸውን ተከትሎ ለብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾችን መልምሎ ወደ ውድድር ለመግባት ፌድሬሽኑ መቸገሩን ተከትሎ ከማጣሪያው ውጪ መሆንን መርጧል፡፡ እንደምንጮቻችን ገለፃ ከሆነ የኬንያ እግርኳስ ፌድሬሽን ከውድድሩ ውጪ መሆኑን በይፋ ለሚዲያ በቅርቡ እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል፡፡

የኢትየጵያ ብሔራዊ ቡድን በአንደኛው የማጣሪያ ዙር ከናይጄሪያ ጋር ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *