የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2010 የውድድር ዘመን ነገ በተመሳሳይ ሰአት በሚደረጉ ሶስት ጨዋታዎች ይጀመራል፡፡ ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከልም አርባምንጭ ስታድየም ላይ የሚደረገው የአርባምንጭ ከተማ እና መቐለ ከተማ ጨዋታ ዋና ዋና ነጥቦችን በዚህ ፅሁፍ ተመልክተናል፡፡
አርባምንጭ ከተማ ከወትሮው የተለየ ክረምትን አሳልፎ ለሊጉ ውድድር ዝግጁ ሆኗል፡፡ በአካባቢው በሚገኙ ተጫዋቾች እና አሰልጣኝ ተገድቦ የቆየው አርባምንጭ ለመጀመርያ ጊዜ የውጪ ዜጋ ተጫዋቾችን በማስፈረም እንዲሁም የቀድሞው የሐረር ሲቲ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማርያምን በአሰልጣኝነት ሹሟል፡፡ አመለ ሚልኪያስ እና ታደለ መንገሻን የለቀቀው ቡድን ሶስት የውጪ ዜጋ ተጫዋቾችን ጨምሮ 6 አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል፡፡
በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ በፕሪምየር ሊጉ የሚካፈለው መቐለ ከተማ በሊጉ በርካታ ግዢ ከፈጸሙ ክለቦች ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ከከፍተኛ ሊጉ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደረገው ሽግግር አካል የሆኑ ተጫዋቾቹን የሸኘ ሲሆን በፕሪምየር ሊጉ ረጅም ጊዜ የቆዩ ተጫዋቾች እና 5 የውጪ ዜጎችን አካቶ አመቱን የሚጀምር ይሆናል፡፡ መቐለ ቡድኑን በአዳዲስ ተጫዋቾች ከማዋቀሩ በተጨማሪ ከ1 ወር በፊት ቡድኑን በተረከቡት አሰልጣኘ ዮሀንስ ሳህሌ ይመራል፡፡
አሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማርያም በንግድ ባንክ አሰልጣኝነታቸው በተደጋጋሚ የተገበሩት የ4-1-4-1 አሰላለፍ ቀዳሚ ምርጫቸው እንደሚሆን በአሸናፊነት ባጠናቀቁት የደቡብ ካስቴል ዋንጫ ላይ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ አምና ጠንካራ የነበረውና የግብ እድል በመፍጠር ረገድ የተሻለ የነበረው የአማካይ ክፍል ዘንድሮ ከስብስቡ በመነሳት በኳስ ቁጥጥር የተሻለ ቡድን ይዞ እንደሚቀርብ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የቡድኑ ድክመት የሆነው የግብ ማስቀጠር ችግርን ሊቀርፉ የሚችሉ ዝውውሮችን በማድረጉ ምናልባትም የፊት መስመሩ ካለፉት ጊዜያት የተሻለ ሊሆን ይችላል፡፡
በተቃራኒው መቐለ ከተማ አመዛኙን የቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅት ወቅት ከቡድኑ ጋር ያሳለፉት አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊትን ያሰናበተ ሲሆን በአሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ አማኝነት የመጨረሻውን አንድ ወር ሲዘጋጅ ቆይቷል፡፡ የቡድን ስብስቡ በበርካታ አዳዲስ ተጫዋቾች የተዋቀረ እና በቂ የዝግጅት ጨዋታዎች ያላደረገ እንደመሆኑ አሰልጣኝ ዮሀንስ ምን አይነት አቀራረብ ሊኖራቸው እንደሚችል መገመት አዳጋች ነው፡፡
በጨዋታው በአርባምንጭ በኩል አምበሉ አማኑኤል ጎበና እና ተከላካዩ ተመስገን ካስትሮ በጉዳት ጨዋታው የሚያመልጣቸው ሲሆን ከመልቀቂያ ጋር በተያያዘ ሙሉ ለሙሉ ዝውውሩ ሳይጠናቀቅ የቆየው ላኪ ሳኒ ለጨዋታው ዝግጁ ነው ተብሏል፡፡ በመቀለ ከተማ በኩል ደግሞ ወሳኙ የቡድኑ አጥቂ እና የከፍተኛ ሊጉ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ባለፈው እሁድ የተሸለመው አማኑኤል ገብረሚካኤል ለብሔራዊ ቡድኑ በመጠራቱ ጨዋታው ያመልጠዋል፡፡