​ኢትዮጵያ ቡና ከ ሲዳማ ቡና | ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መጀመሪያ ሳምንት ላይ እንዲከናወን ፕሮግራም ተይዞለት የነበረው የኢትዮጵያ ቡና እና የሲዳማ ቡና ጨዋታ ነገ 11:30 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ይካሄዳል። በዚህ ጨዋታ ላይ የተወሰኑ ነጥቦችን ለማንሳት ወደድን።                                                          
ባሳለፍነው ሳምንት የሊጉን የመጀመሪያ ጨዋታ ያደረገው ኢትዮጵያ ቡና ከመከላከያ ጋር ተገናኝቶ በሳሙኤል ሳኑሚ ብቸኛ ጎል ማሸነፍ ችሏል። ሲዳማ ቡና በበኩሉ ወደ ወልዋሎ በማቅናት ያለግብ አቻ ሲለያይ ሁለተኛው ሳምንት ላይ አርባምንጭን ባስተናገደበት ጨዋታም በአንድ ጎል ሲመራ ቆይቶ 74ኛው ደቂቃ ላይ በተገኘችው የአዲስ ግደይ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ነጥብ መጋራት ችሎ ነበር።
በአዲሱ አሰልጣኝ ኮስታዲን ፓፒች ስር የመጀመሪያ ጨዋታውን ባለፈው ቅዳሜ ያደረገው ኢትዮጵያ ቡና ከተለመደው አቀራረቡ ለየት ብሎ ታይቷል። በተለይ ቡድኑ የ4-1-3-2ን አሰላለፍ ይዞ ጨዋታውን መጀመሩ በዚህም ከፊት ሁለት አጥቂዎችን ማጣመሩ ያልተጠበቀ ነበር። ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታውን ያሸንፍ እንጂ የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴው ከተለመደው ተዳክሞ ታይቷል። በተለይም ከክሪዚስቶም ንታንቢ ፊት እና ከአጥቂዎቹ ጀርባ የሚኖረው የቡድኑ እንቅስቃሴ በራሱ የመቀባበያ ክፍተቶችን ሲያሳጣው ይታያል። በማጥቃት ሂደት ውስጥ የአማካዮቹ ያለቅጥ የተጠጋጋ ቦታ አያያዝ ኳስ የሚመሰርቱበትን መንገድ የሚያወሳስብ እና ተጋጣሚ እንቅስቃሴውን ለማቋረጥ እንዳይቸገር የሚያደርግ ነው። ከቀደመው የቡድኑ የጨዋታ አቀራረብ በተለየ መልኩ የመስመር አጥቂዎችን ሲጠቀም ያልተስተዋለው የአሰልጣኝ ፓፒች ቡድን የሜዳውን ስፋት ለመጥቀም የመስመር ተከላካዮቹ ሚና እንደወትሮው እስከተጋጣሚ የግብ ክልል ድረስ የዘለቀ አለመሆኑ በርካታ የግብ እድሎችን እንዳይፈጥር ሲያደርገው ተስተውሏል። በተለይ መከላከልን የመጀመሪያ ምርጫቸው የሚያደርጉ ቡድኖች ሲገጥሙት እነዚህ ነጥቦች ቡድኑ በቀላሉ ጎሎችን እንዳያገኝ ሊያደርጉት ይችላሉ። የነገ ተጋጣሚው ሲዳማ ቡናም ከነዚህ ቡድኖች መሀከል አንዱ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ቡድኑ ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን አቻ ወጥቶ ሊጉን መጀመሩ ይህን ጨዋታ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ እንዲገባ ሊያደርገው ቢችልም ሶስተኛ ተከታታይ የአቻ ውጤት ለማስመዝገብ መከላከሉ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ይጠበቃል። 

ሲዳማ ቡና አምና የነበረውን ጠንካራ የቡድን ውህደት የዝውውር መስኮቱ ካሳሳበት በኋላ ከባድ የውድድር አመት ሊገጥመው እንደሚችል የተገመተ ነበር። በመስመር አማካዮቹ ወደ መሀል እየጠበበ የሚመጣ የማጥቃት አጨዋወት ላይ የተመሰረተው ሲዳማ ቡና የማጥቃት አጨዋወት አመርቂ የሆነ አይመስልም። ቡድኑ በሁለት ጨዋታዎች ያገኛት አንድ ግብም በፍፁም ቅጣት ምት የተገኘች መሆኗ ግብ የማስቆጠር ችግሩን የሚያሳይ ነው።  የአሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህ ቡድን በነገው ጨዋታ ወደ ኃላ ተስቦ ከመከላከል ባለፈ ከመስመሮች በሚነሱ እና እንደ ፍፁም ተፈሪ ባሉ አማካዮቹ በሚጣሉ ቀጥተኛ ኳሶች ላይ ተመስርቶ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚሞክር ይጠበቃል።  ይህን በማድረግ ግብ ለማግኘትም ቡድኑ ለመልሶ ማጥቃት የተመቹ ዕድሎች ሲፈጠሩ ወደ ተጋጣሚው የሜዳ ክልል ለመድረስ እጅግ ፈጣን መሆን ይጠበቅበታል። የፊት አጥቂው ባዬ ገዛኸኝም የእንቅስቃሴዎቹ ዋነኛ መዳረሻ ሆኖ ከኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች ጋር የሚፋለም ይሆናል። በጨዋታው የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ቡና የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን የቡድኑ የአማካይ መስመር ተሰላፊዎች የሚጠቀሙበት መንገድ በቁጥር በርክቶ እና ለተከላካይ ክፍሉ ቀርቦ ሊጫወት በሚችለው የሲዳማ የአማካይ ክፍል ፈተና እንደሚገጥመው ይገመታል። ሁለቱ የፊት አጥቂዎች ማናዬ ፋንቱ እና ሳሙኤል ሳኑሚ ብዙ ክፍት ይሆናል ተብሎ በማይጠበቀው ጨዋታ ላይ የሲዳማን የተከላካይ መስመር የሚጋፈጡ ይሆናል።

በሲዳማ ቡና በኩል የተሰማ የጉዳት ዜና ባይኖርም የኢትዮጽያ ቡናው አስቻለው ግርማ ከጉዳት ባለማገገሙ ለጨዋታው እንደማይደርስ ታውቋል። ከዚህ ውጪ ለሴካፋ ዝግጅት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የሚገኙት አበበ ጥላሁን እና አዲስ ግደይ ከሲዳማ ቡና እንዲሁም ሳምሶን ጥላሁን እና መስዑድ መሀመድ ከኢትዮጵያ ቡና በነገው ጨዋታ ላይ ለክለባቸው አገልግሎት የሚሰጡ ይሆናል።

ጨዋታውን በዋና ዳኝነት የሚመራው ፌደራል ዳኛ ጌቱ ተፈሪ ሲሆን ፌደራል ዳኛ አያሌው አሰፋ እና ፌደራል ዳኛ ጌቱ ተጫኔ በረዳት ዳኝነት እንዲሁም ፌደራል ዳኛ ኢቢራሂም አጋዥ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *