​ሪፖርት | ፋሲል በሜዳው የመጀመርያ ድሉን አስመዝግቧል

የስድስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አምስት ጨዋታዎች ዛሬ ክልል ላይ ሲደረጉ ጎንደር ላይ ወላይታ ድቻን ያስተናገደው ፋሲል ከተማ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ ሰንጠረዡ አናት ተጠግቷል።
አፄዎቹ በሜዳቸው በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች አስደናቂ የድጋፍ አሰጣጥ መመልከት የተለመደ ቢሆንም  ዛሬ በስታዲየም የታየው የድጋፍ አሰጣጥ ግን እጅግ አስደናቂ ነበር። በሜዳቸው ሁለተኛ  ጨዋታቸውን ያደረጉት ፋሲሎች በጨዋታው ተሽለው መንቀሳቀሳቸው የታየ ሲሆን በተቃራኒው ወላይታ ዲቻዎች ብዙውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በራሳቸው የሜዳ ክፍል በመገደብ ተከላክለው ተጫውተዋል።

በኢብራሂም አጋዥ የመሀል ዳኝነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ብቻ 7 የማዕዘን ምት ያገኙት ፋሲሎች ጨዋታው እንደተጀመረ ተጭኖ በመጫወት ተጋጣሚያቸውን ሲያስጨንቁ ቢታይም በመጨረሻው የማጥቃት ሲሶ ሲደርሱ ግን ፍሬያማ አጨራረስ ሲያሳዩ አልተስተዋለም። በ36ኛው ደቂቃ ራምኬል ሎክ በግምት ከ20 ሜትር ርቀት አክርሮ የመታው ኳስ በፋሲሎች በኩል ለግብ የቀረበ አጋጣሚ የነበረ ሲሆን በተቃራኒው ዲቻዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ምንም ሙከራ ሳያደርጉ ወጥተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ አጨዋወታቸውን በመጠኑም ቢሆን ቀይረው የገቡት ባለሜዳዎቹ በመጀመሪያው አጋማሽ ከሚያደርጉት የመስመር ላይ እንቅስቃሴ ውጪ መሃል ለመሃል ለማጥቃጥ ሲሞክሩ ታይቷል። ይህም እንዲሆን ከኳስ ጋር ምቾት ያላቸውን ተጨዋቾች ያስገቡ ሲሆን በንፅፅር ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ እንዲንቀሳቀሱ አድርጓቸዋል። በዚሁ የጨዋታ ሂደት በ57ኛው ደቂቃ ሰዒድ ሁሴን እና ኤርሚያስ ኃይሉ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል የደረሱ ቢሆንም ግዙፉ አጥቂ ፍሊፕ ዳውዚ ሳይጠቀምበት ኳሷ ወደ ውጪ የቀረችው ኳስ አጼዎቹን ቀዳሚ ማድረግ የምትችል አጋጣሚ ነበረች።

ጫናቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ፋሲሎች በ66ኛው ደቂቃ ኤርሚያስ ኃይሉ ከመዓዘን ያሻገረውን ኳስ ተከላካዩ አይናለም ኃይሉ በግንባሩ በመግጨት ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ መሆን ችለዋል።

ከጎሉ መቆጠር በኋላ እምብዛም አስደንጋጭ የሆነ የጎል ሙከራ ያልተስተናገደ ሲሆን እንደ መጀመሪያው አጋማሽ  የአቻ ውጤት ይዞ ለመውጣት በሚመስል መልኩ ተከላክለው ሲጫወቱ የነበሩት ድቻዎች በ63ኛው ደቂቃ ብቻ የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ በተመስገን ዱባ አማካኝነት አግኝተው ሚኬል ሳማኪ አድኖባቸዋል።

ፋሲል ከተማ ከዛሬው ድል በኋላ በ9 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ሲችል ተጋጣሚው ወላይታ ድቻ በስድስት ጨዋታ 5 ነጥቦችን ብቻ በመያዝ 13 ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

ምንተስኖት ጌጡ – ፋሲል ከተማ

“ጨዋታው ጥሩ ነበር። በደንብ በልጠን ነው የተጫወትነው። ከመጀመሪያው አጋማሽ ጀምሮ ተጭነን ለመጫወት ሞክረናል። ብዙ የግብ እድሎችንም መፍጠር ችለናል። ነገር ግን የግብ አጋጣሚዎችን ወደ ግብነት የመቀየር ችግር ነበረብን።

“ተጋጣሚያችን በጥልቀት ነበር ሲከላከሉ የነበረው። እነሱን ለማስከፈት ተቸግረን ነበር።

“ቡድኔ ዛሬ ባሳየው እንቅስቃሴ ተደስቻለሁ። ነገር ግን ጎሎችን የማስቆጠር ችግራችንን ማሻሻል እንዳለብን አምናለሁ።”

መሳይ ተፈሪ – ወላይታ ድቻ

“በጨዋታው ተበልጠናል። ፋሲሎች ከኛ በተሻለ ተንቀሳቅሰዋል። ከሜዳችን ውጪ እንደመጫወታችን ተከላክለን ለመጫወት ሞክረናል። ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ እንዳሰብነው አልተጫወትንም። በተለይ ለማጥቃት ባሰብነው መንገድ አልተጫወትንም።

“አሁን ባለው ሁኔታ ጨዋታዎች በሰላም ተጀምረው መጠናቀቃቸው ራሱ ትልቅ ነገር ነው። ደጋፊዎች በጨዋታ ተደስተው እየጨፈሩ ሲወጡ ማየት ደስ ይላል። በተለይ የፋሲል ደጋፊዎች የሚገርሙ ደጋፊዎች ናቸው። አምናም እኛ እዚህ መጥተን 2-0 ባሸነፉበት ጊዜ በጥሩ መልኩ ነበረ አስተናግደው የሸኙን። ዛሬም ቡድናቸውን የሚደግፉበት መንገድ ድንቅ ነበር።

“ሊጉን የጀመርንበት መንገድ ጥሩ አይደለም። ነገር ግን በእርግጠኝነት ከዚህ በኋላ ያሉ ጨዋታዎችን እንደምናሸንፍ እተማመናለሁ።”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *