አርባምንጭ ከተማ ከወልዋሎ ፤ ድሬዳዋ ከ አዳማ ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማ የሊጉ መሪ ወልዋሎን አስተናግዶ 1-1 አቻ ሲለያይ ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከ አዳማ ከተማ አቻ ተለያይተዋል።

​አርባምንጭ 1-1 ወልዋሎ

አርባምንጭ ላይ የተደረገው የአርባምንጭ እና ወልዋሎ ጨዋታ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተቆጠሩ ጎሎች እና ውዝግቦች ታጅቦ 1-1 ተጠናቋል። 

ለረጅም ደቂቃዎች ያለ ጎል በዘለቀው ጨዋታ 85ኛው ደቂቃ ላይ ከሙሉአለም ጥላሁን የተቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ወግደረስ ታዬ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት የአንተነህ መሳ መረብ ላይ አስቆጥሮ ወልዋሎን መሪ ሲያደርግ  በመደበኛው ክፍለ ጊዜ መገባደጃ ዮናታን ከበደ ወደ ግብ የመታትን ኳስ በወልዋሎ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁ ቅጣት ምት ላኪ ሰኒ አስቆጥሮ አርባምንጭ ከተማን ከመሸነፍ ያዳነል ጎል አስቆጥሯል።

አስተያየቶች

ፀጋዬ ኪማርያም – አርባምንጭ ከተማ 

” ጨዋታው ቀላል እንደማይሆን ገምተን ነበር። ያን በሜዳ ላይ አግኝተነዋል። ሆኖም ቡድኔ በእንቅስቃሴ ረገድ ጥሩ ነበር። ደጋፊዎች ያሰሙት ተቃውሞን እቀበለዋለው። አንድ ደጋፊ ውጤት ይፈልጋል። ያን ነው እነሱ ዛሬ ያሰሙት። አሁንም ቢሆንም ግን ሊታገሱን ይገባል።”

ብርሀኔ ገ/እግዚአብሔር – ወልዋሎ

“በጨዋታው አልተከፋውም። ውጤቱም ተገቢ ነው። ከሜዳ ውጭ እንደመጫወታችን አንድ ነጥብ ማሳካት ትልቅ ድል ነው።  መሪ ነን። ይህን ይዘን በተፎካካሪነት እንዘልቃቀን”

ድሬዳዋ ከተማ 0-0 አዳማ ከተማ

እምብዛም አመርቂ የጨዋታ እንቅስቃሴ ባልታየበት ጨዋታ የመጀመርያ አጋማሽ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ሲታይበት በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋች ለውጥ አድርገው የገቡት ድሬዳዋዎች የተሻለ እንቅስቃሴ እና የጎል ሙከራ ማድረጋቸውን በስፍራው የነበሩ ጋዜጠኞች ሲገልፁልን የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊዎች በክለባቸው እንቅስቃሴ ደስተኛ ባለመሆናቸው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ላይ ተቃውሟቸውን ማሰማታቸው ታውቋል። 

የሁለቱም ክለቦች አሰልጣኞች ከጨዋታው በኃላ ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጡትን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

ዘላለም ሽፈራው – ድሬዳዋ ከተማ

“ዛሬ ሙሉ በሙሉ በልጠን ተጫውተናል። ባለፉት ጨዋታወች የግብ እድል መፍጠር ነበር ችግራችን። ዛሬ ግን  ጫና ፈጥረን ተጫውተናል። ሆኖም ያገኘነውን እድል ወደ ጎል መቀየር አቅቶናል። በቀጣይ ይህን ለመቅረፍ እንሞክራለን”

ተገኔ ነጋሽ – አዳማ ከተማ

“ጨዋታው ጥሩ ነበር። ከሜዳችን ውጭ በመጫወታችን ነጥብ ይዞ ለመምጣት ጥረት አድርገናል። እነሱ የተሻሉ ነበሩ። በቡድኔ ጉዳት እና በብሔራዊ ቡድን ምክንያት ወሳኝ ተጫዋቾች እንደማጣታችን ውጤቱ አያስከፋኝም”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *