​ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | አአ ከተማ ከሽረ መሪነቱን ተረክቧል

አአ ከተማ 1-0 ሽረ እንዳስላሴ
(በዳንኤል መስፍን)

በሁለቱ የምድቡ አናት ላይ በተቀመጡ ክለቦች መካሕ ዛሬ 09:00 መድን ሜዳ ላይ የተካሄደው ጨዋታ በስፍራው የነበረውን የስፖርት ቤተሰብ ያዝናና እንቅስቃሴ የታየበት ቢሆንም የተሳካ የጎል ሙከራ ለማድረግ 36 ደቂቃ ያህል መጠበቅ አስፈልጎ ነበር።  የጎል ሙከራ በማድረግም እንግዶቹ ሽሬዎች ቀዳሚዎች ነበሩ ከመስመር የተሻገረውን ልደቱ ለማ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ብረቱን ታኮ የወጣበት አጋጣሚ የሚያስቆጭ ነበር።

ከእረፍት መልስ አአ ከተማ ተሽሎ የታየበት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሆኖ ታይቷል። ተቀይሮ ገብቶ  መልካም እንቅስቃሴ ማድረግ የቻለው እንዳለማው ታደሰ ከቀኝ መስመር በጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ የተሻገረለትን ኳስ 53ኛው ደቂቀ ላይ ወደ ጎልነት በመቀየር አአ ከተማን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ከጎሉ መቆጠር በኋላ አአ ከተማዎች ውጤት  ለማስጠበቅ ወደ ኋላ ማፈግፈጉን ተከትሎ ሽሬዎች የአቻነት ጎል ፍለጋ ሙሉ ለሙሉ ወደ ማጥቃት ቢሻገሩም ጎልና መረብን ማገናኘት ተስኗቸው ታይተዋል። በተለይ በመጨረሸዎቹ ደቂቃዎች ሁለት ግልፅ የማግባት አጋጣሚዎች አግኝተው የአአ ተከላካይ ፋሲል ጌታቸው ከመስመር ያወጣው እና ፍሬው ጌታሁን ያዳናት ኳስ ሽሬዎችን አቻ መሆን የሚችሉበት አጋጣሚ ነበር።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የዕለቱ ዳኛ የሰጡት ጭማሪ ደቂቃ አነስተኛ ነው በማለት ሽረዎች ተቋማቸውን አሰምተዋል። በዕለቱ ጨዋታ ከሽሬ ብሩክ ገ/አብ ከአአ ከተማ ምንያምር ዼጥሮስ በጨዋታው ላይ ድንቅ አቋማቸውን ያሳይተዋል።

ውጤቱን ተከትሎ አአ ከተማ በምድብ ሀ  በሦስት ጨዋታ ሦስቱንም በማሸነፍ  አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በዘጠኝ ነጥብ ምድቡን እየመራ ይገኛል።

ቡራዩ ከተማ 2-0 ባህርዳር ከተማ

(በአምሀ ተስፋዬ)

ቀዝቀዝ ባለ የጨዋታ እንቅስቃስ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ መኩራ በማድረግ ቡራዩ ከተማ ቀዳሚ ነበር። በ8ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ከድር ወደ ግብ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው አድኖበታል፡፡ በ19ኛው ደቂቃ ላይ ባለሜዳዎቹ በአጭር ኳስ ቅብብል ወደ ባህርዳር የግብ ከልል ደርሰው ሚሊዮን ይሳማዬ ቢሞክርም በግብ ቀኝ ከፍል ወጥታበታለች፡፡ በ31ኛው ደቂቃ በግራ ክንፍ የተሻማውን ኳስ ይትባረክ ሀብታሙ በግንባሩ ገጭቶ ግብ ጠባቂው ምንተስኖት ያዳነበት ሙከራም በቡራዩ በኩል የሚጠቀስ ሙከራ ነበር።

39ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ከድር በቀኝ መስመር ሁለት ተጫዋቾችን አልፎ ወደ ሳጥን በመግባት በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት ለውጦታል፡፡ ከግቡ በኋላ በ45ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ከድር በድጋሚ ሌላ ለ.መልካም የግብ አጋጣሚ አግኝቶ አልተጠቀመበትም።

በባህርዳር በኩል 4ኛው ደቂቃ ላይ ወድሜነህ ደረጀ በሳጥን ውስጥ ተገፍቶ ወደቆ በዝምታ  ታልፏል በሚል ቅሬታቸውን የገለፁ ሲሆን በ15ኛው ደቂቃ ላይ በሳለአምላክ ተገኝ አማካኝነት የመጀመሪያ ሙከራ አድርገዋል፡፡ 41ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ በግንባሩ ገጭቶ ግብ ጠባቂው እንደምንም ሲያድንበት በ44ኛው ሙሉቀን ታሪኩ  ከሚኪያስ ግርማ የተሻገረውን ኳስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

ከዕረፍት መልስ ባህር ዳር ከተማዎች ተጭነው በመጫወት የአቻነት ግብ ለማግኘት ጥረት ያደረጉ ቢሆንም በሁለተኛው አጋማሽ ውጤታቸውን በማስጠበቅ ላይ ያተኮሩት ቡራዩዎችን ሰብረው ጎል ማስቆጠር አልቻሉም። በአንፃሩ ቡራዩ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት የግብ እድሎችን ሲፈጥሩ ቆይተው 81ኛው ደቂቃ ላይ ሚሊዮን ይሳማዬ ባስቆጠረው ጎል ልዩነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ አድርገዋል።

ጨዋታው በቡራዩ 2-0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ሜዳው ለዳኞች ነፃነት የማይሰጥና ደጋፊን ከ ሜዳው የሚለይ የሚለይ አጥር አለመኖሩ ዳኞች ላይ ተፅዕኖ ሲፈጥር ተስተውሏል፡፡

በሌሎች ጨዋታዎች ለገጣፎ ላይ ለገጣፎ ሱልልታ ከተማን አስተናግዶ በዘካርያስ ከበደ እና በሐብታሙ ፍቃዱ ግቦች 2-0 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ፌደራል ፖሊስ ከ ከኢኮስኮ ፣ ሰበታ ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን እንዲሁም ወሎ ኮምቦልቻ ከየካ ክፍለ ከተማ በተመሳሳይ የ1-1 አቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ደሴ ላይ ደሴ ከተማ ከ ነቀምት ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ደግሞ ያለምንም ግብ ሲጠናቀቅ አክሱም ላይ ሊደረግ የነበረው የአክሱም ከተማ እና አወረስኮድ ጨዋታ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል።


የደረጃ ሰንጠረዡን ሊንኩን በመጫን ይመልከቱ | LINK 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *