መቐለ ከተማ እና መከላከያ ከሜዳቸው ውጪ አሸንፈዋል

ከሰባተኛው ሳምንት የሊጉ መርሀ ግብሮች መሀከል ወደ ዓዲግራት እና ሶዶ ያመሩት መከላከያ እና መቐለ ከተማ በተመሳሳይ 1-0 ውጤት በማሸነፍ ደረጃቸውን አሻሽለዋል።

ወላይታ ድቻ 0-1 መቐለ ከተማ

በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወላይታ ድቻዎች በማጥቃቱ ብልጫን ይዘው ቢታዩም በመልሶ ማጥቃት የተዋጣላቸው መቐለዎች ገና በጊዜ ግብ ማስቆጠር ችለዋል፡፡ ግቧም 11ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ሜዳ አጋማሽ ላይ አማኑኤል ገ/ሚካኤል በረጅሙ ያሻገራትን ኳስ በአግባቡ በመቆጣጠር ጋይስ አፖንግ የወላይታ ድቻን የመሀል ተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ ያስቆጠራት ነበረች።

ጨዋታውን አስመልክቶ የሁለቱ ክለቦች አሰልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ – ወላይታ ድቻ 

“በተከላካዮቻችን ያለመረጋጋት እና አለመናበብ ምክንያት በሁሉም ጨዋታዎች ቀድመው በመጀመሪወቹ ደቂቃዎች የሚቆጠሩብን ግቦች ዋጋ እያስከፈሉን ነው። የምናገኛቸውንም አጋጣሚዎች ወደ ጎል መቀየር አልቻልንም። ዛሬም ያ ነገር ነው የታየው። በተለይ ዛሬ ጃኮ ፣ ዳግም ፣ እና በረከት እንዲሁም ከጨዋታው በፊት የነበሩ ጉዳቶች ዋጋ አስከፍለውናል። ጃኮ የተጎዳብን ቅያሪ ከጨረስን በኃላ ስለነበር አማራጭ አሳጥቶናል ፡፡ ማሸነፍ ግን የምንችለው ጫወታ ነበር፡፡ አሁን ያለብንን የተከላካይ ክፍተት በቀጣይ ከሲዳማ ላለብን ጨዋታ በሚገባ አርመን እንቀርባለን፡፡

አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ – መቐለ ከተማ 

“ዛሬ ተሳክቶልናል። ድቻ ጠንካራ እና አስቸጋሪ ቡድን መሆኑን ስለምናውቅ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ሲጫወቱ ተመልክተናል። የቱ ጋር ድክመት እንዳለባቸው እና ጠንካራ ጎናቸውም የቱ እንደሆነ በሚገባ ተመልክተናል። ስለሆነም ዛሬ ግብ ካስቆጠርን ኃላውን መዝጋት ነበር አላማችን። ያም እድለኛ አድርጎናል። በድሉም ኮርቻለሁ። የልጆቼ የማሸነፍ ስሜት እና ተነሳሽነትም አስደስቶኛል፡፡

ወልዋሎ 0-1 መከላከያ

የሊጉ መሪ እና የመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ሁለቱን ክለቦች ባገናኘው ጨዋታ መከላከያ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን አሳክቷል። በ33ኛ ደቂቃ ላይ አማኑኤል ተሾመ በቀኝ መስመር የላካትን ኳስ የወልዋሎው ግብ ጠባቂ ዘውዱ መስፍን እና ተከላካዩ በረከት ተሰማ መሀከል በተፈጠረ አለመናበብን በመጠቀም ምንይሉ ወንድሙ አስቆጥሮ ጦሩን አሸናፊ አድርጓል። 70ኛው ደቂቃ ላይ የወልዋሎው እንየው ካሳሁን እና የመከላከያው ሳሙኤል ሳሊሶ እርስ በእርስ በተሰናዘሩት ቡጢ ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ሁለቱንም በቀጥታ ቀይ ከሜዳ አስናብተዋቸዋል።

ጨዋታውን አስመልክቶ የሁለቱ ክለቦች አሰልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ብርሀኔ ገ/እግዚያብሔር – ወልዋሎ ዓ.ዩ

“ዛሬ ተሸንፈናል። በአሰልጣኝነት ዘመኔ ምክንያት መስጠት አልፈግም። ዛሬ ግን ያስገድደኛል። አይን ያወጡ ጫናዎች ተደርገውብናል። በሜዳችን ዳኛው ያደረገብን ተፅዕኖ ለማመን ከብዶኛል። እነሱ አንድ ሙከራ አደረጉ አገቡ። እኛ ብዙ ጥረት አድርገን እየተኙ ጨረሱብን። ለዛ መልስ መስጠት ዳኛው አልቻሉም። አንድ ዳኛ ሳይሆን ሶስቱም ዳኛ ተመሳሳይ በደል አድርሰውብናል። የዛሬ ፊልም ቢቀረፅ ጥፋተኛው ማን እንደ ነበር ይለይ ነበር። በተለይ ረዳት ዳኛ ክንዴ ሙሴ የሚሰራው ስህተት ለማንም የሚጠቅም አይደለም፡፡ በውጤቱ ግን አዝኛለሁ ”

ምንያምር ፀጋዬ – መከላከያ 

” ከሜዳችን ውጭ እንደመጫወታችን በጣም ጥንቃቄ አድርገን ነው የተጫወትነው። እነሱ እንደ መሪ እኛ ኃላ እንዳለ ቡድን ሆነን ነው የተገናኘነው። እነዚህን ነገሮች ይዘን ወደ ሜዳ ገባን። ከሜዳ ውጭ እንደ መጫወታችን ግብ ላለማስተናገድ ነበር አንደኛ አላማችን። ባገኘነው አጋጣሚ ደሞ ማስቆጠር ካገባን መከላከል ነበር አላማችን ያን አድርገናል፡፡ እነሱ ለማጥቃት ሲመጡ እኛ ደሞ ካገባን በኃላ ለመከላከል ተገደናል። ልጆቻችን በሜዳ ላይ ይጎዱብን ነበር። ሲተኙ በተቃራኒ ቡድን ጫና እያደረባቸው ነበር። አስጠብቀን ግን ወጥተናል። ውጤቱ ይገባናል። ተከላክለን ብናጠቃም የሳሙኤል በቀይ መውጣት ግን አላሳመነኝም። የተመታው እሱ ነበር፡፡ በቀጣይ ያጣነውን የአሸናፊነት መንፈስ ለማምጣት እንጥራለን፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *