አርባምንጭ ከተማ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምን አሰናበተ

በክረምቱ የአርባምንጭ ከተማ አሰልጣኝ በመሆን ተሹመው የነበሩት ፀጋዬ ኪዳነማርያም ቡድኑን ለ8 ሳምንታት ከመሩ በኋላ ከኃላፊነታቸው በዛሬው እለት ተነስተዋል። 

አርባምንጭ ከተማ በውድድር ዘመኑ ካደረጋቸው 8 ጨዋታዎች አንድ ድል ብቻ አስመዝግቦ በደረጃ ሰንጠረዡ 14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን አሰልጣኝ ፀጋዬም ቡድኑ በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያስተናግዱ ቆይተዋል።

ዛሬ የክለቡ ቦርድ ምሽት ላይ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባው የክለቡ ቴክኒክ እና የቦርድ አመራሮች ባቀረቡት ሪፖርት መሰረት ክለቡ ለውጤቱ መጥፋት እንደምክንያት አሰልጣኙን ተጠያቂ በመደረጋቸው እንዲሰናበቱ መወሰነ ታውቋል።

የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ፀጋዬ ጌሌ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ለአሰልጣኝ ፀጋዬ መሰናበት የደጋፊዎች ተቃውሞ እና ወጤት መጥፋት ምክንያቶች እንደሆኑ ተናግረዋል። ” ይህን ውሳኔ ስንወስን ጫናዎች በዝተውን የደጋፊዎችን ጥያቄ ለማክበር ነው። ለቡድኑ ላደረጉት ነገር በሙሉ ምስጋናችን የላቀ ነው። በውጤት ባለመታጀቡ ብቻ እንድንለያይ አድርጎናል። መልካሙን ሁሉ ለአሰልጣኙ በክለቡ ስም እንመኛለን። ክለቡ ውስጥ በርካታ መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች አሉ። ጣልቃ ገብነት እና ያልተገቡ ጥቅሞች አንዳንድ ግለሰቦች ይፈልጋሉ። በቀጣይ ከዚህ ሊቆጠቡ ይገባል” ብለዋል።
አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም ከክለቡ ከተለያዩ በኋለመ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደተናገሩት በክለቡ የአሰልጣኝነት ስራነሰ የሚያከብዱ በርካታ ችግሮች እነደነበሩ ገልፀዋል። 

” ይህ የአሰልጣኝነት ባህሪ ነው። መባረር መቀጠር ያለ ነው። ቡድኑ ላይ ብዙ ችግሮች ነበሩ። ከዚህ ቀደም ብዙ ከኔ በፊት ያልተፈቱ ችግሮች ነበሩ። ትጥቅ እና የደሞዝ ክፍያ ሳይሟላ ሳይሟላ ውጤት መጠበቅ ከባድ ነው። በአንዳንድ ግለሰቦች ጣልቃ ገብነትም ስራዬን በአግባቡ እንዳልሰራ ተደርጌያለሁ። ይህ ሁሉ ለክለቡ አሳውቄ ነበር። በቀጣይ ማረፍ ካለብኝ አርፋለሁ አልያም በ10 ወይም በ15 ቀን ውስጥ ክለብ መያዝ አይከብደኝም።” ብለዋል።
አርባምንጭ ከተማ አዲስ አሰልጣኝ እስኪሾም በረዳት አሰልጣኙ በረከት ደሙ እየተመራ የሚቀጥል ይሆናል። የቀድሞ የክለቡ አማካይ በረከት አምና ጫማውን ሰቅሎ የጳውሎስ ፀጋዬ ረዳት በመሆን ሲሰራ የቆየ ሲሆን የአሰልጣኝ ጳውሎስን ስንበት ተከትሎ የመጨረሻዎቹ 9 የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት መምራቱ የሚታወስ ነው።

የቀድሞ የአርባምንጭ ጨርቃጨርቅ ኮከቦች የነበሩት እዮብ ማለ (ሀዲያ ሆሳዕና) ወይም መሳይ ተፈሪ (ወላይታ ድቻ) የክለቡ አሰልጣኝነት መንበር በቀጣይ እንዲረከቡ ክለቡ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ ተሰምቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *