ሪፖርት | አዳማ ከተማ ከሲዳማ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል

የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት በእለተ እሁድ በአዳማ አበበ በቂላ ስታድየም አዳማ ከተማን ከሲዳማ ቡና ያገናኘው ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ሁለቱም ቡድኖች ለዛሬው ጨዋታ ከመድረሳቸው አስቀድሞ አዳማ ላይ በአምስተኛ ሳምንት የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታ ላይ ሀዋሳ ከተማን 1-0 ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ ያደረጋቸውን ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ያጠናቀቀቀው አዳማ በሜዳው ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚጠቀምበት ጨዋታ ይሆናል ተብሎ ሲገመት በአንፃሩ ሲዳማ ቡና ከአቻ እና ሽንፈት የሰባት ሳምንት የሊጉ ጉዞ በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት ይርጋለም ላይ ወላይታ ድቻን 3-1 በማሸነፍ የአመቱ የመጀመርያ ድሉን በጨበጠ ማግስት በተነቃቃ መንፈስ ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡

በአዳማ ከተማ በኩል ሱሌማን መሀመድ በጉዳት ፣ ኤፍሬም ዘካርያስን በሀዘን ምክንያት በዛሬው ጨዋታ ያላካተተ ሲሆን ሲዳማ ቡና በአንፃሩ ባዬ ገዘኸኝን በቅጣት ሳያካትት ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡

ጨዋታው በሜዳ ላይ በነበረው እንቅስቃሴ ለተመልካች አዝናኝ ከመሆን ይልቅ አሰልችነቱ ያመዘነ፣ ተደጋጋሚ የዳኛ ፊሽካ የበዛበት፣ በአሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ የታየበት ሆኖ ማለፉ የጨዋታው አጠቃላይ ገፅታ ሆኖ አልፏል፡፡

ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ የአዳማው ግብ ጠባቂ ጃኮ ፔንዜ ለጨዋታ የለበሰው ማልያ ከተቃራኒ ቡድን ጋር ይመሳሰላል በማለት የዕለቱ ዳኞችና ኮሚሽነሩ እንዲቀይር በወሰኑት ውሳኔ ምክንያት ባለሜዳ በመሆናችን አያወልቅም ፣ ቅድመ ጨዋታ ላይ የሚለብሰው ማልያ ታቷል በማለት በተፈጠረው ክርክር ጨዋታው መጀመር ካለበት 10 ደቂቃ ዘግይቶ ጃኮም ማሊያውን ቀይሮ ጨዋታው ሲጀመር ከእረፍት መልስ የተከለከለውን ማልያ በድጋሚ መልበሱና እንዲጫወት መደረጉ አግራሞትን ጭሯል።

ፌ/ዳኛ ዳንኤል ግርማይ በመራው ጨዋታ የመጀመርያው አጋማሽ ባለ ሜዳዎቹ አዳማዎች ተሽለው የቀረቡበት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሲሆን 8ኛው ደቂቃ ላይ በዕለቱ በቀኝ መስመር በኩል ከተከላካይ መስመር እየተነሳ በማጥቃቱ ላይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው በረከት ደስታ ያሻገረለትን ታፈሰ ተስፋዬ ወደ ጎል መቶት ለጥቂት የወጣበት አጋጣሚ የጨዋታ የመጀመርያ ሙከራ ሆኖ ተመዝግቧል። ባልተደራጀ ሁኔታም ቢሆን አዳማዎች ወደ ፊት በማጥቃት ቢጫወቱም ለጎል የቀረበ ሙከራ ማድረግ ሲሳናቸው ተስተውሏል። 13ኛ ደቂቃ ላይ 23 ሜትር ርቀት ላይ የተሰጠውን ቅጣት ምት ዳዋ ሁቴሳ መቶት ግብ ጠባቂው ፍቅሩ ወዴሳ ያዳነውን አግዳሚው ገጭቶ ሊወጣ ችሏል።

በጨዋታው የነበረውን ፈጣን እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ በሚሰሩ አላስፈላጊ ጥፋቶች ምክንያት ዳኛው በሚነፉት ፊሽካ የተነሳ ጨዋታው ወደ አሰልቺነት ሊቀየር ሲችል ከጨዋታው እንቅስቃሴ ይልቅ ጥቂት የማይባሉ የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች የሚያሰሙት ዝማሬ እና የአካል እንቅስቃሴ በጨዋታው ተሰላችቶ ለነበረው ተመልካች ጥሩ መዝናኛ ሆኖ ማለፍ ችሏል፡፡ 30ኛው ደቂቃ ላይ ሲዳማ ቡናዎች ወንድሜነህ አይናለም ከርቀት አክሮ የመታውን ኳስ ጃኮ ፔንዛ ሲተፋው አዲስ ግደይ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ጎልነት ቢቀይረውም ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ ነው በሚል መሻሩ ሲዳማ ቡናዎችን ውሳኔው አስከፍቷቸዋል። ብዙም ሳይቆይ ጃኮ ከግብ ክልሉ ወቶ በእግሬ እጫወታለው ብሎ የተሳሳተውን ስህተት አብዱልለጢፍ መሀመድ ሳይጠቀምበት የቀረው የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር።

ጨዋታው ከአሰልቺነት እንቅስቃሴ ወቶ በፍጥነት ወደ ጎል በሚደረግ ጥቃት ውስጥ አዳማዎች 35ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ በግል ጥረቱ ከአዳማ የሜዳ ክፍል ኳስ እየገፋ ተከላካዮችን በማለፍ ሳጥን ውስጥ ለተስፋዬ በቀለ የሰጠውን ተስፋዬ በቀለ ለዳዋ ሁቴሳ ሰጥቶት ዳዋ ወደ ጎልነት በመቀየር አዳማን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ወንድሜነህ አይናለም ከሳጥን ውጭ አክርሮ የሚመታቸው ኳሶች ኢላማቸውን የጠበቁ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ግብ ጠባቂው ጃኮ ላይ ስራ አብዝቶበት ውሏል፡፡ 39ኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት መቶ እንደምንም ያዳነበት ያዳነበት ኳስም በጉልህ ተጠቃሽ ነበር። ጎሉ ከተቆጠረባቸው በኋላ ጫና እንደመፍጠራቸው ሲዳማዎች 43ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ ወንድሜነህ አይናለም አክርሮ የመታውን ኳስ ጃኮ ሲተፋው ትርታዬ ደመቀ አግኛቶ ጃኮፍን አልፎ የሲዳማ አቻነት ጎል በአዝናኝ ሁኔታ አስቆጥሯል። በተመሳሳይ ሁኔታ 45ኛው ደቂቃ ላይ እንዲሁ ወንድሜነህ አይናለም ከሳጥን ውጭ አክርሮ መቶ ጃኮ እንደምንም ያወጣው ሌላ ጎል ሆኖ ሊቆጠር የሚችል አጋጣሚ ነበር።

ከእረፍት መልስ እንግዶቹ ሲዳማዎች ከእረፍት በፊት ከነበራቸው ደካማ እንቅስቃሴ ተሽለው የቀረቡ ሲሆን ለዚህ ማሳያ 49ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ገዛህኝ ከመሀል ሜዳ ገፍቶ ወደ አዳማ የግብ ክልል በመግባት በጥሩ ሁኔታ የመታውን ኳስ የተከላካዮች ሽፋን አነስተኛ በመሆኑ የተነሳ ስራ በዝቶበት የነበረው ግብ ጠባቂ ጃኮ በአስደናቂ ሁኔታ አድኖበታል። የሲዳማዎች የማጥቃት ሀይል እያመዘነ በመጣበት አጋጣሚ በቡድናቸው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እየተሰላቹ የመጡት የአዳማ ከነማ ደጋፊዎች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ ላይ ተቋማቸውን በማሰማት ” አሰልጣኝ ይቀየር ሰለቸን ” በማለት ሲናገሩ ተደምጠዋል። በዚህ ተቃውሞ ውስጥ አዳማዎች ሆነው የተሳካ የኳስ ንክኪ እንኳን ማድረግ ሲያቅታቸው 65ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሁቴሳ በግሩም ሁኔታ መቶት ግብጠባቂው ፍቅሩ ወዴሳ ያዳነበት 76ኛው ደቂቃ ላይ ከመአዘን የተሻገረውን ሙጂብ በግንባሩ መቶት ፍቅሩ ያዳነው የጎል ሙከራ ከሚጠቀሰው ውጭ ይህ ነው ተብሎ የሚነገር በአዳማ በኩል የጎላ የጎል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

ሲዳማዎች ከአዳማ የተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም ጎል አስቆጥሮ አሸንፎ ከመውጣት ይልቅ ጥንቃቄን መምረጣቸው የወሰዱትን የጨዋታ ብልጫ ወደ ጎልነት ሳይቀይሩት ጨዋታው 1 – 1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ከጨዋታው መጠናቀቅም በኋላ በአሰልጣኙ ላይ የተነሳው ተቃውሞ አይሎ ደጋፊዎች ከአዳማ የቡድን አመራሮች ጋር ተነጋግረው ተለያይተዋል። ውጤቱን ተከትሎ አዳማ በሜዳውም ከሜዳው ውጭ የሚያስመዘግበውን የአቻ ውጤት ተከትሎ ደረጃ ሰንጠረጁ 12 ነጥብ በመያዝ ደረጃውን በማሻሻል 6ኛ ደረጃ ሲቀጥል ሲዳማ ቡናዎች በ9 ነጥብ 11 ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት

ም/አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል – አዳማ ከተማ

ጨዋታው ተመጣጣኝ ነበር፡፡ በሰራነው የትኩረት ማጣት ስህተት ጎል ሊቆጠረብን ችሏል እንጂ ጨዋታውን ተቆጣጥረን ለመውጣት ሞክረን ነበር፡፡ ያው እግር ኳስ በመሆኑ በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል። ደጋፊው በዚህ ሜዳ ድል ለምዷል ከዚህ በመነሳት ውጤት ይዘን ባለመውጣታችን እንዳያችሁት ተከፍቶ ወጥቷል።

አሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህ – ሲዳማ ቡና

ጨዋታው ብዙም ውበት የለውም፡፡ ይህም ባለ ሜዳው የሚጫወተው በረጃጅም ኳስ በመሆኑ ይህን ወደ መሬት አውርደን ለመጫወት ተቸግረን ነበር፡፡ በመጀመርያው አጋማሽ ብልጫ ቢወሰድብንም በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ መንቀሳቀስ ችለን ነበር፡፡ የዛሬውን ጨዋታ አሸንፈናል ፤ ያስቆጠርነው ጎል ለምን እንደተሻረ አልገባኝም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *