በድንቅ አቋም ላይ የሚገኘው አቤል ያለው…

በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ በቅርቡ ብቅ ካሉ እና ነጥረው ከወጡ ወጣቶች መካከል አንዱ የሆነው አቤል ያለው ድንቅ የውድድር ዘመን እያሳለፈ ይገኛል። 4 ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ የሚገኘውና በንፅፅር ለወጣቶች የተሻለ የመጫወት እድል እየሰጠ በሚገኘው ደደቢት የዘንድሮ ስብስብ ጎልቶ መውጣት የቻለ አጥቂ ነው።

የአቤል ያለው የግርኳስ ህይወት በራሱ አንደበት 

(በዳንኤል መስፍን)

” ኳስ የጀመርኩት 22 ሾላ ሰፈር ነው። ብዙ ሳልቆይ ወደ አቃቂ ማዞርያ ክለብ በመሄድ በከፍተኛ ዲቪዝዮን ተጫወትኩኝ። በመቀጠል በ17 አመት በታች ሻምፒዮና የአዲስ አበባ ምርጥ ወስጥ መካተት ችያለሁ። ይህም ወደ ሐረር ሲቲ ለማምራት በር ከፍቶልኛል። በሐረር ሲቲ ለሁለት ዓመት ከመሀመድ ኢብራሂም (ኪንግ) ጋር ያሳለፍኩት ጊዜ እንድሻሻል ረድቶኛል። በመቀጠል ወደ ደደቢት ዮሐንስ ሳህሌ ይዞኝ መጣ። እዚህም እስካሁን ጥሩ ነገር እያሳለፍኩ ነው፡፡ ከሐረር ሲቲ ጋር ብሔራዊ ሊግ (አንደኛ ሊግ) እየተጫወትኩ በማሀል ነው ወደ ደደቢት የመጣሁት። ወደ ደደቢት ከመጣው በኃላ የመጀመሪያዋቹ ወቅት ላይ ብዙ የመሰለፍ እድል ስላላገኘሁ ወደ ፋሲል አምርቼ ነበር። በቆይታዬም ጥሩ ልምድ አግኝቼ ወደ ደደቢት ተመልሻላው፡፡ በቆይታዬም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡

 ” እኔ መስመር ላይ እና አጥቂ ላይም  መጫወትን እችላለው። ለኔ ዋናው ነገር መጫወቴ ነው፡፡ ማንም ተጫዋች ጠንክሮ ከሰራ ትልቅ ቦታ ይደርሳል። እኔ ገና ምንም አልጀመርኩኝም። ገና ብዙ መስራት አለብኝ።  

” አርአያ የማደርገው ተጫዋች ጌታነህ ከበደ ነው። ለሱ የተለየ እይታም ነበረኝ። በተለይ ጎል የሚያስቆጥርበት መንገድ በጣም ያስደስተኛል። 

“ጎሎችን የማስቆጥረው በቡድን አጋሮቼ እገዛ ነው። እኔ ለብቻዬ ምንም ያደረኩት ነገር የለኝም። ከዚህም በኃላ የተሻለ እገዛ ያደርጉልኛል ብዬ አምናለው።

 ” አድናቆት ብዙ ተጫዋቾችን ያዘናጋል። ይህ ነገር እንዳይከሰትም በርካታ ተጫዋቾች ይመክሩኛል። እኛ ቡድን ውስጥ ብዙ ሲነየር ተጫዋቾች አሉ። ከነሱም በቂ ልምድ እየቀሰምኩ ነው። በአጠቃላይ እኔ የምፈልገው ስራዬን በዝምታ እና ራሴን በመጠበቅ መስራት ነው። 

አቤል ያለው ዘንድሮ  

አምና በደደቢት ማልያ የሊግ ጨዋታ በመደበኛነት ማድረግ ያልቻለው አቤል በፋሲል መለያ በሁለተኛው ዙር ተጫውቶ 1 ጎል ማስቆጠር ችሏል። ዘንድሮ ወደ ደደቢት ተመልሶ በ7 የሊግ ጨዋታዎች 5 ጎሎች ሲያስቆጥር ለብሔራዊ ቡድኑ 3 የሴካፋ ጨዋታዎች አድርጎ 2 ጎሎች አስቆጥሯል። 

የአቤልን ብቃት ያጎላው የደደቢት የቅርፅ ለውጥ 

(በዮናታን ሙሉጌታ) 

በአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ስር አመቱን የጀመረው ደደቢት አሁን ያለውን አሸናፊ ቡድን ለመገንባት ሳምንታት ወስደውበታል።  በዚህ ሂደት ውስጥ ቡድኑ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት 4-4-2 እና 4-2-3-1 አሰላለፎችን በተጠቀመባቸው አጋጣሚዎች አቤል በሁለተኛ አጥቂነት እና በብቸኛ አጥቂነት በመሰለፍ አንድ ግብ ማስቆጠር ሲችል በማጥቃት ሂደቱ ላይም ጉልህ አስተዋፅዖ ሲያበረክት ቆይቷል። ነገር ግን ደደቢት አራት ተከታታይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ በቻለበት የ4-3-3 አሰላለፍ ውስጥ የመስመር አጥቂነት ሚና የተሰጠው አቤል በእነዚህ ወቅቶች አራት ግቦችን ከማስቆጠሩም በላይ በቀሪዎቹ ጎሎች ላይ የነበረው ተሳትፎም የጎላ ነው። ተጫዋቹ ያለውን ከፍተኛ ፍጥነት እና የግል ክህሎት በመጠቀም ከመስመር ተነስቶ ተጨዋቾችን በማለፍ በቀላሉ የተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ የመግባት ችሎታው የተሰጠው ሚና በልኩ የተሰፋ እንዲሆን አድርጎታል። ከእዚህ ባሻገር አቤል የተጋጣሚ ተከላካዮችን ቅብቅብል ለማፈን የሚያደርገው ጫና የቡድኑን የፊት መስመር አስፈሪነት ከፍ ያደረገው ሲሆን እንደ አጥቂ የሚያገኛቸውን ኳሶች በቀጥታ ወደ ግብ ከመሞከር ባለፈ ከአጋር አጥቂዎች ጋር ያለው የቅብብል ስኬትም በቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ ሁሌም ተሳታፊ እንዲሆን አስችሎታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *