ኢትዮጵያ ቡና እና ጋቶች ፓኖም በውል ጉዳይ መስማማት አልቻሉም

ከሩሲያው ክለብ አንዚ ማካቻካላ ጋር የነበረውን የ3 ዓመት ውል በስምምነት አፍርሶ ወደ ሃገሩ የተመለሰው ጋቶች ፓኖም ወደ ቀድሞ ክለቡ ኢትዮጵያ ቡና ሊያደርገው የነበረውን ዝውውር እክል ገጥሞታል፡፡ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ እና ክለቡ ዛሬ ለመጨረሻ ድርድር ቢቀመጡም መስማማት ሳይችሉ ቀርተዋል፡

ጋቶች ወደ ኢትዮጵያ ቡና ለመመለስ ቅድሚያ መስጠቱን ተከትሎ ቡናማዎቹ ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ ከተጫዋቹ ጋር ድርድር ማድረግ ጀምረው ነበር፡፡ ሆኖም ዛሬ የክለቡ የቦርድ ፕሬዝደንት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ እና የደጋፊዎች ማህበሩ አባላት በተገኙበት በተካሄደው ድርድር ጋቶች ያቀረበው የደሞዝ ጥያቄ በክለቡ ውድቅ ሆኗል፡፡ ተጫዋቹ ከታክስ የተጣራ 250ሺ ብር የጠየቀ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ 130ሺ ብር (ታክስ ጨምሮ) ለአንድ አመት እንዲሁም 150ሺ ብር (ታክስን ጨምሮ) ለሁለት ዓመት ለማስፈረም ውል አቅርቦለት ነበር፡፡ ክለቡ በተጨማሪ ተጫዋቾቹ በየትኛውም ግዜ የውጪ ሃገር የመጫወት እድል ሲያገኝ በነፃ መልቀቅንም ጨምሮ አቅርቧል፡፡
ሁለቱ አካላት በዚህ ጉዳይ ላይ ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም፡፡ ኢትዮጵያ ቡና የተጠየቀውን ደሞዝ አሁን ላይ ባለው የክለብ አቅም መክፈል እንደማይችል የተጠቆመ ሲሆን በሃገሪቱ የተጫዋቾች ዝውውር እና በክለቡ ተጫዋቾች ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ተፅዕኖ ተዳምሮ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳማይችል ተገልጿል፡:

ለእረፍት ጀርመን የሚገኘው የጋቶች ወኪል ዴቪድ በሻ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት ሌሎች ክለቦች የእናስፈርምህ ጥያቄን ለመቀበል በራቸው ክፍት መሆኑን ገልጿ አማካዩ በኢትዮጵያ የመጫወት እድሉ ዝቅ ያለ መሆኑን ተናግሯል፡፡ “አዎ ከቡና ጋር ስምምነት ላይ መድረስ አልቻልንም፡፡ ሌሎች አማራጮችን እያየን ነው አንዱም ግብፅ ነው፡፡ እኔ እንደማስበው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚቆይ አይመስለኝም፡፡”
ዴቪድ ግብፅ ቀጣዩ የጋቶች መዳረሻ መሆን እንደምትችል ከመጠቆም ውጪ ከየትኛው የግብፅ ክለብ ጋር ድርድር እንዳደረጉ ከመናገር ተቆጥቧል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና እና ጋቶች በውል ጉዳይ አምና በተመሳሳይ ድርድሮችን ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን ከአምናው በተለየ የዘንድሮው ያልተሳካ ሆኖ አልፏል፡፡ ተጫዋቾቹን ለማስፈረም ወላይታ ድቻ እና መቀለ ከተማ ፍላጎት ያሳዩ ሌሎች ክለቦች ሲሆኑ አሁን ላይ በሚወጡት መረጃዎች የውጪ ሃገራት ክለቦች የተጫዋቹ ቀጣይ ማረፊያ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *