​” ብዙ የመጫወት እድል ማግኘቴ በራስ መተማመኔን አሳድጎታል ” ዳዋ ሁቴሳ 

የአዳማ ከተማው አጥቂ ዳዋ ሆቴሳ ባለፉት 4 ጨዋታዎች 5 ጎሎችን በማስቆጠር በወቅታዊ ድንቅ አቋም ላይ ይገኛል። ዳዋ ባለፈው እሁድ አዳማ ከተማ ቡናን 2-1 አሸንፎ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ ባደረገበት ጨዋታ አንድ ጎል በቅጣት ምት ያስቆጠረ ሲሆን ከጨዋታው በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል።

በጥሩ አቋም ላይ ትገኛለህ.. 

በጥሩ ወቅታዊ አቋም ላይ እገኛለሁ። አቅሜ እየተሻሻለ በጥሩ ሁኔታ እገኛለው። ብዙ የመጫወት ዕድል ባገኘህ ቁጥር በራስ መተማመንህ እየጨመረ ነው የሚሄደው። ከዚህ ከደም ይልቅ እዚህ የበለጠ የጨዋታ እድል አግኝቼ እየተጫወትኩ ነው። ይህ በራስ መተማመኔን እና አቋሜም አሻሽሎታል። ደጋፊውን እንደምታየው ከእኛ ጋር ነው። በተለይ ለእኔ ጎልም ስለማገባ ፣ ጥሩ ስለምንቀሳቀስ አይን ውስጥ ገብቻለሁ።

ከመሰለፍ እድል ጋር በተያያዘ በቅዱስ ጊዮርጊስ ያለፉትን አመታት ብዙም ዕድል አለማግኘትህ በእግርኳስ ህይወትህ ተፅዕኖ ፈጥሮብህ ነበር? 

በቅዱስ ጊዮርጊስ በቂ የመሰለፍ እድል አለማግኘቴ ተፅዕኖ አድርጎብኛል። አቅም እንዳለኝ አውቃለው። ዋናው የራስህ እምነት ነው ጥሩ የሚያደርግህ። ጊዮርጊስ በነበረኝ ቆይታ በተቀያሪ ወንበር እና ከጨዋታ ውጪ የምሆንበት ጊዜ ነበር። ይህ ደግሞ ራሴን ወጥቼ እንዳላሳይ አድርጎኛል። አሁን ላይ ግን አቅሜን እያሳየው ነው። በእግርኳስ ህይወቴም ዘንድሮ ደስተኛ ነኝ።

በተከታታይ ጨዋታዎች ጎል እያስቆጠርክ ነው።  ከዚህ በኋላ በዚህ አቋምህ ስለመቀጠል ምን ታስባለህ ?

ሁሌ የተለመደው በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት እነ ጌታነህ ከበደ እና ሳላዲን ሰኢድ ናቸው ሲሆኑ የሚታወቀው። እኔም አሁን ባለኝ አቅም የምቀጥል ከሆነ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ የመሆን ትልቅ አላማ አለኝ። ይህንንም አሳካለው ብዬ አስባለሁ።

ዳዋ በሊጉ የመጀመርያ 5 ጨዋታዎች በጉዳት ፣ ቅጣት እና የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ምክንያት 2 ጨዋታ ብቻ ያደረገ ሲሆን ከ8ኛ ሳምንት ጀምሮ ባደረጋቸው 4 ጨዋታዎች 5 ጎሎች ማስቆጠር ችሏል። 

የቅጣት ኳስ አጠቃቀምህ እየተሻሻለ ፤ ጎልም እያስቆጠርክ ነው። ይህን እንዴት አዳበረረከው?
ሁሌም በልምምድ ወቅት የቅጣት ምት አመታት እለማመዳለሁ። በቅርብ ርቀት የሚገኙ ቅጣት ምቶች እንድጠቀምም ኃላፊነት ተሰጥቶኛል። ለዛም ይመሰልኛል ዘንድሮ በጨዋታ ብቻ ሳይሆን በቅጣት ምት ጎል እያስቆጠርኩ ጠንካራ ሙከራም እያደረኩ ነው። ከዚህ በኃላም ይህንን ለማድረግ ጠንክሬ እሰራለው።

የምትጫወትበት ቦታ እንደ ጨዋታው ይቀያየራል። አንዳንዴ ወደ መስመር አጥቂነት ሌላ ጊዜ ቀጥተኛ አጥቂ ትሆናለህ በየትኛው ቦታ  ብትሰለፍ ትመርጣለህ?

ሁለቱም ይመቸኛል። በሁለቱም በኩል መጫወት እችላለው ፤ በተለይ የፊት አጥቂ ሆኜ ስጫወት የበለጠ ይመቸኛል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *