ተስፋዬ በቀለ ይባላል። ዘንድሮ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የ20 አመት በታች ቡድን ወደ ዋናው ቡድን ካደጉ አምስት ወጣቶች መካከል አንዱ ነው። ብዙም የመሰለፍ እድል ባያገኝም ተቀይሮ በመግባት ተስፈኛ ተጫዋችነቱን እያሳየም ይገኛል። ከቡድን አጋሩ እና አርአያው ከሚያደርገው በኃይሉ አሰፋ ጋር በአጨዋወቱ ከመመሳሰሉ ባሻገር ” ቱሳ ” የሚለው ቅፅል ስሙንም የሚጋራው ተስፋዬ የወደፊቱ ኮከብ እንደሚሆን ፍንጭ እያሳየ የሚገኝ የመስመር አጥቂ ነው። ሶከር ኢትዮዽያ በዚህ ሰምንት የተስፈኛ ተጫዋቾች አምዷ ከተስፋዬ ጋር በእግርኳስ ህይወቱና የወደፊት እቅዱ ዙርያ ቆይታ አድርጋለች።
ትውልድና እድገትህ የት ነው? እግርኳስ መጫወትስ እንዴት ጀመርክ ?
ተወልጄ ያደኩት ቂርቆስ ሰፈር ነው። ለአካባቢው ቅርብ የሆነ ሜዳ ባይኖርም ከሰፈራችን ራቅ ብሎ ካባ ተብሎ በሚጠራ ሜዳ የሰፈር ልጆች ተሰብስበን እየሄድን እንጫወት ነበር። ከቤተሰቤ ኳስ የሚጫወት ሰው ባይኖርም ሰፈሬ ብዙ ኳስ ተጫውተው ያለፉ ተጨዋቾች መኖራቸውና ቤታችን ለአአ ስታድየም ቅርብ በመሆኑ በተለያየ ጊዜ ኳስ ለማየት እንመጣ ነበር። ያም ተጫዋች እንድሆን አነሳስቶኛል።
ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ17 አመት በታች ቡድን እንዴት ልታመራ ቻልክ ?
መስቀል አደባባይ በአሰልጣኝ መስፍን የሚመራ ፕሮጀክት እየሄድን እንሰለጥን ነበር። 2005 ላይ የዕውቀት ምንጭ የተሰኘ ቡድን ውስጥ ገብቼ በክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ውድድር ላይ ተሳትፌ ባሳየሁት አቋም ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሲ ቡድን ብመረጥም ሲዘገይብኝ ወደ ለአንድ አመት ኢትዮዽያ ንግድ ባንክ ሲ ቡድን ተጫውቻለሁ። ባንክ በነበርኩበት ቆይታም ለአአ ምርጥ መጫወት ችያለው። 2006 ላይ በአሰልጣኝ በላቸው ኪዳኔ ጥሪ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲ ቡድን ካመራሁ በኋላ ለሦስት አመት በቡድኑ ቆይቼ በ2009 ከ20 አመት በታች ቡድኑን መቀላቀል ችያለሁ።
በ20 አመት በታች አንድ አመት ብቻ አሳልፈህ ዘንድሮ ወደ ዋናው ቡድን አድገሀል። ምን አይነት ስሜት ፈጠረብህ ?
የልጅነት ህልም ወደ ሆነ ክለብ መግባት ቀላል አይደለም ። የመጫወት ፍላጎትህ ይጨምራል ፣ በአካል እና በአዕምሮም ታድጋለህ። የምትሰለጥነው በትላልቅ አሰልጣኞች ነው። አብረውህ የሚጫወቱ ተጫዋቾችም ትልልቅ ስም ያላቸው ናቸው። ከእነሱ ብዙ የምትማራቸው ነገሮች አሉ። በአጠቃላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሚባል ትልቅ ክለብ ውስጥ አድጎ መጫወት በራሱ እድለኝነት ነው። እስካሁን ባለኝ ነገር ሁሉ ደስተኛ ነኝ።
በፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎች ላይ ተቀይረህ በመግባት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እያደረክ ትገኛለህ. ቆይታህ ምን ይመስላል?
ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁን በጣም ደስተኛ ነኝ። ቅዱስ ጊዮርጊስን በሚያህል ትልቅ ክለብ ለሰከንድ መጫወት በራሱ የሚፈጥረው ስሜት ቀላል አይደለም። እኔ የተሻለ እንድሰራ ሲኒየሮቹ ምክር ይሰጡኛል ፤ ትክክል ያልሆነ ስራ ስሰራ አስተካክል ብለው ያርሙኛል። ከኔ ጋር ያደግነው ታዳጊዎችን በሙሉ ትልቅ ተጫዋች እንድንሆን ይመክሩናል። ከዚህ ውጭ በሚሰጠኝ እድል ክለቤን ለመጥቀም እሰራለሁ። በቶሎ ቋሚ እንደማልሆን አውቃለው ፤ ሆኖም እራሴን ለማሳደግ ጠንክሬ እሰራለሁ ።
በትልልቅ ክለቦች እንኳን ለታዳጊ ተጨዋቾች ቀርቶ ልምድ ላላቸውም በቶሎ የቋሚነት እድል ማግኘት ከባድ ነው። ሆኖም በዛ ደረጃ ራስህን ስለማሳደግ ምን ታስባለህ ?
አሁን ቅድሚያ የምሰጠው ቋሚ ስለመሆን አይደለም ፤ ጊዜው ገና ነው። ራሴን በትልቅ ደረጃ ለማሳደግ ጠንክሬ መስራትን ፣ አሰልጣኞቼ የሚሰጡኝን ስልጠና በአግባቡ መቀበል ነው የምፈልገው። ሁሉም ነገር የሚወሰነው በውስጥህ ባለው ጥንካሬ ነው። እኔ ገና ብዙ የሚቀረኝ ታዳጊ ነኝ። ሁሌም ለተሻለ ነገር መስራት አለብኝ። በሚሰጠኝ እድል ደግሞ የምችለውን ሁሉ ለማድረግ እጥራለሁ።
የኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተመርጠህ ተጫውተሀል?
በአሰልጣኝ አጥናፉ ጥሪ ተደርጎልኝ ነበር። ሆኖም እሰከመጨረሻው ከቡድኑ ጋር ዝግጅት አድርጌ 22 ተጨዋቾች በመጨረሻ ቀርተን የMRI ምርመራ ላይ እድሜዬ 17 አመት ሞልቶት ስለነበር መጫወት የሚቻለው ደግሞ ከ17 አመት በታች በመሆኑ ሳልጫወት ቀርቻለው ።
ወደ ዋናው ቡድን የሚያድጉ ተጫዋቾች አብዛኛዎቹ ማለት ባይቻልም ከተወሰነ ጊዜ በኃላ የነበራቸው መልካም ባህሪ እና ተነሳሽነት እየተለወጠ ወደ አለመታዘዝ ያመራሉ ይባላል። አንተ በዚህ ረገድ ያለህ ሀሳብ ምንድነው ?
እኔ የማቀው እግርኳስ መጫወትን እንዳልጀመርኩ ነው። ማንም ሰው ሰርቶ ጠንክሮ ትላንት ከነበረው ደረጃ ራሱን ከፍ ካላደረገ በዚህ ቡድን ውስጥ እንደማይቆይ ጠንቅቄ አውቃለው ። እንኳን ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫውተህ የትም ክለብ ከሄድክ ባህሪህን ጠብቀህ ራስህን ካላሻሻልክ የትም መድረስ አትችልም። እኔ ወደፊት የማስበው በቅዱስ ጊዮርጊስ መጫወት ብቻ አይደለም ወደ ውጭ ወጥቼ ሁሉ መጫወት አስባለው።
ምሳሌ የምታደርገው ተጨዋች ማን ነው ?
በጣም ይገርምሀል ስታድየም ጨዋታ ካለ አልቀርም። ሁሌ እየመጣው ኳስ አያለው። ስመጣ ደግሞ ሁለት ተጨዋቾችን ማየት በጣም ያስደስተኛል። እነሱም በኃይሉ አሰፋ እና ምንያህል ተሾመ ናቸው። ሁሌም የእነሱን ጨዋታ ማየት ያስደስተኛል። አሁን አጠገቤ በጣም ከምወደው በኃይሉ ጋር በመጫወቴ ትልቅ ደስታ ይሰማኛል። ብዙ ነገር ይመክረኛል ያስተምረኛል ።
በአጨዋወትህ ከኃይሉ ጋር ከመመሳሰልህ በተጨማሪ ቅፅል ስምህም (ቱሳ) ከተጫዋቹ ተመሳሳይ ነው። ይህ ከየት ሊመጣ ቻለ?
ባንክ ሲ ቡድን እየተጫወትኩ በኃይሉ (ቱሳ) ለደደቢት ይጫወት ነበር። እኔም የሱን ጨዋታ ለማየት በጣም እፈልግ ስለነበር ‘ ዛሬ የቱሳ ጨዋታን አያለው ‘ ብዬ እየሮጥኩ እሄድ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ የምጫወተው ቦታ እና አጨዋወቴን አነፃፅረው ቱሳ ብለው ይጠሩኝ ጀመር። አሁንም ድረስ መጠርያ ቅፅል ስሜ ሆነ ቀረ ማለት ነው።
ክለቦች በታዳጊዎች ላይ እምነት እንዲያሳድሩ የምታስተላልፈው መልክት አለ ?
ክለቦች ታች ድረስ ወርደው ቢያዩ በጣም ደስ ይለኛል። በፈጣሪ ፍቃድ እኛ እዚህ ቆመናል። ከእኛ የተሻሉ ልጆች ታች አሉ። ወርደው ቢያዩ በጣም ደስ ይለኛል።
በመጨረሻም …
እዚህ ደረጃ እንድደርስ ለረዱኝ ቤተሰቦቼ ፣ አሁንም ያሉትንም ታች የነበሩትን የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኞች እና ደጋፊዎችን በሙሉ ከልብ አመሰግናለው።