​ወላይታ ድቻ እስከ ውድድር አመቱ መጨረሻ በአሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ ይመራል

ወላይታ ድቻ ያለፉት 4 ጨዋታዎችን በጊዜያዊ አሰልጣኝነት የመራው አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሀን እስከ ውድድር አመቱ መጨረሻ ድረስ በቋሚነት ሾመ።

ወላይታ ድቻ ከ9 አመታት የክለቡ ቆይታ በኋላ የተሰናበቱት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን በመተካት የክለቡ ከ17 አመት በታች አሰልጣኝ የነበረው ዘነበ ፍሰሀን በጊዜያዊነት በዋና አሰልጣኝነት መሾሙ ይታወሳል። በቀጣይ ክለቡን ሌሎች በርካታ አሰልጣኞች ይረከባሉ እየተባለ ቢነገርም የክለቡ ቦርድ ትላንት ምሽት ባደረገው ስብሰባ አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ እስከ አሁን ክለቡን ይዞ ባደረጋቸው አራት የሊጉ ጨዋታወች በሜዳው ሁለት ጨዋታ በድል ሲያጠናቅቅ ከሜዳው ውጭ ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡና እና ወልዋሎ ጋር ነጥብ በመጋራት የክለቡን ደረጃ ማሻሻሉ አመርቂ ሆኖ በመገኘቱ ወላይታ ድቻን እስከ ውድድር ዘመኑ በዋና አሰልጣኝነት እየመራ እንዲዘልቅ ወስኗል፡፡ የአሰልጣኝ ዘነበ ውልም ከዚህ አመት መጨረሻ በኋላ በሚያስመግበው ውጤት መሰረት ታይቶ በቀጣዩ አመት የተጨማሪ ኮንትራትን እንደሚቀርብለትም ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡
ወላይታ ድቻን በቋሚነት የተረከበው አሰልጣኝ ዘነበ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት በክለቡ ውሳኔ ደስተኛ እንደሆነ ገልጿል።  ” እንዲህ አይነት ውሳኔ ላይ በመድረሳቸው ደስተኛ ነኝ። ስፈልገው የነበረውን ነገር አግኝቻለሁ። በቅድሚያ በቀጣይ ጊዜያት ክለቡን የተሻለ ደረጃ ላይ ማድረስ እፈልጋለሁ። ተጫዋቾቼ ባላቸው አቅም ላይ የተመረኮዘ ስራ ሰርተን በአፍሪካ መድረክም ሆነ በፕሪምየር ሊጉ በቀጣይ ባሉን ጨዋታዎች ላይ ውጤታማ ለመሆን እንጥራለን። በተለይ በአፍሪካ መድረክ የመጀመርያ ተሳትፏችን እንደመሆኑ በአዕምሮ ረገድ እንዲዘጋጁ እየሰራን እንገኛለን።  በሁለተኛው ዙር ደግሞ ባለን ክፍተት የተሻሉ የሚባሉ ተጨማሪ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ ለማምጣት አቅደናል። ” ብሏል።

ከ1985 – 1995 በቆየው የተጫዋችነት ዘመኑ በሀዋሳ ከተማ ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ኢትዮጵያ መድን እና ወንጂ ስኳር እንዲሁም በኢትዮጵያ ታዳጊ እና ወጣት ቡድኖች ተጫውቶ ያሳለፈው አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሀ በጉልበት ጉዳት ምክንያት ማቆም ከሚገባው ጊዜ ቀደም ብሎ ነበር ከእግርኳስ አለም የተገለለው። በተጫዋችነት ዘመኑ የነበረውን አስከፊ ጊዜ በአሰልጣኝነት ዘመኑ ስኬት በማስመዝገብ የመርሳት ህልም እንዳለውም ለሶከር ኢትዮጵያ ገለጿል።
ወላይታ ድቻ በፕሪምየር ሊጉ 13ኛ ሳምንት የፊታችን ቅዳሜ በሜዳው ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲያስተናግድ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ከዛንዚባሩ ዚማሞቶ ክለብ ጋር የካቲት 4 ላይ ከሜዳው ውጭ የሚያደርግ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *