​ኢትዮዽያ ቡና ከሦስት ተጫዋቾቹ ጋር በስምምነት ተለያየ 

ኢትዮዽያ ቡና በዘንድሮ አመት በሊጉ በሚኖረው ውድድር ቡድኑን በተሻለ ያጠናክራሉ ተብሎ በማሰብ ከ10 በላይ ተጫዋቾችን ቢያስፈርምም አመዛኞቹ አዳዲስ ተጫዋቾች በታሰበው መልኩ አገልግሎት እየሰጡ አይገኙም።

ዘንድሮ ፊርማቸውን ካኖሩ ተጫዋቾች መካከል የመስመር ተጫዋቹ አብዱሰላም ኑሩ እንዲሁም አጥቂዎቹ በረከት ይስሐቅ እና ማናዬ ፋንቱ ከቡድኑ ጋር በስምምነት መለያየታቸው የታወቀ ሲሆን ከቅርብ ቀናት ወዲህ ሙሉ ለሙሉ ከቡድኑ ጋር ልምምድ ማቋረጣቸውም ታውቋል ።

አብዱሰላም ወልዋሎ አዲግራት ወደ ኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ እንዲገባ ካስቻሉ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የነበረ ቢሆንም በኢትዮዽያ ቡና በፍጥነት መላመድ ሳይችል ቀርቷል። በቅድመ ውድድር ወቅት ዝግጅት ወቅት በአሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች የተሰጣቸውን የሙከራ ጊዜ ተጠቅመው ፊርማቸውን ያኖሩት በረከት ይስሐቅ (ከድሬዳዋ ከተማ) እና ማናዬ ፋንቱ (ከኤሌክትሪክ) በሊጉ የመጀመርያ ሳምንታት ጨዋታዎች እየተፈራረቁ የመሰለፍ እድል ቢያገኙም በረከት ይስሀቅ አንድ ጎል ከማስቆጠሩ ውጪ ክለቡን የሚያሳምን እንቅስቃሴ ማድረግ አለመቻላቸውን ተከትሎ መለያየታቸው እርግጥ ሆኗል።

በውድድር አመቱ የቡድኑ ሦስተኛው አሰልጣኝ በሆኑት ዲዲዬ ጎሜስ የሚመራው ኢትዮዽያ ቡና በውጪ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮት በመጠቀም የአጥቂ መስመር ተጫዋች የሆኑት ዩጋንዳዊው ቦባን ዚሩንቱሳ እና ሴኔጋላዊው ባፕቲስቴ ፋዬን ማስፈረሙ በተለይ ለሁለቱ አጥቂዎች ከቡድኑ መልቀቅ መነሻ የሆነ ይመስላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *