ስለአለም ዋንጫ የሁለት ቀናት የአዲስ አበባ ቆይታ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠ

የአለማችን ትልቁ የእግር ኳስ መድረክ በሆነው የአለም ዋንጫ አሸናፊ የሆኑ ቡድኖች የሚያነሱት ዋንጫ የውድድሩ ዋና ምልክት እና ሽልማት ነው። 

በጣልያናዊው ሲልቪዮ ጋዛኒካ ዲዛይን የተደረገው እና ምዕራብ ጀርመን በ1974 ካስተናገደችው የአለም ዋንጫ ጀምሮ ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው ይህ ውብ ዋንጫ በቋሚነት በፊፋ ይዞታ ስር የሚቆይ እንዲሁም የውድድሩ አሸናፊዎች ፣ የተመረጡ ግለሰቦች እና የሀገር መሪዎች ብቻ እንዲነኩት ወይም እንዲይዙት የሚፈቀድ በመሆኑ ሌላው የስፖርቱ አፍቃሪ በቀላሉ ሊያገኘው እና በቅርበት ሊመለከተው የሚችልበት አማራጭ አልነበረም። ሆኖም ጀርመን ካስተናገደችው የ2006ቱ የአለም ዋንጫ ወዲህ ከውድድሮቹ መጀመር አስቀድሞ በተመረጡ የአለማችን ከተሞች በመዞር ለህዝቡ እንዲቀርብ ሲደረግ መቆየቱ ለእግር ኳስ አፍቃሪያን በህይወት ዘመን አንድ ጊዜ ብቻ በሚገኝ ዕድል ልዩ ስሜትን ሲፈጥር ቆይቷል። 

ዋንጫው ከወራት በኃላ የሚጀመረውን የ2018ቱን የአለም ዋንጫ አስመልክቶ በመስከረም ወር በአዘጋጇ ሀገር ሩሲያ የጀመረውን ጉዞ ከዚህ በፊት ካደረጋቸው ጉዞዎች ሁሉ ከፍ ባለ ሁኔታ 126 ሺህ ኪሎሜትሮችን በማቆራረጥ በ51 ሃገራት የሚገኙ 91 ከተሞችን እየጎበኘ ይገኛል። የኢትዮጵያችን ዋና ከተማ አዲስ አበባም በፊፋ እና በኮካ ኮላ ኩባንያ አዘጋጅነት እየተካሄደ ባለው በዚህ ጉብኝት ውስጥ ከተካተቱ አስር የአፍሪካ ሀገራት አንዷ በመሆን የዋንጫውን መምጣት በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች።

ዛሬ 08፡00 ሰዓት ጀምሮ በኮካ ኮላ አማካይነት በሒልተን ሆቴል የተሰጠው መግለጫ ይህንኑ የዋንጫውን ጉዞ የተመለከተ ነበር። መግለጫው በኢ.ፌ.ደ.ሪ ወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስቴር ድኤታው አማካሪ የሆኑት አቶ መንግስቱ ሳህሌ ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ ፣ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ አበበ ገላጋይ እንዲሁም የኮካ ኮላ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ቀንድ ብራንድ ማናጀር የሆኑት ወ/ት ትዕግስት ጌቱ ከተለያዩ የሚዲያ አካላት ጋር የተገኙበት ነበር። ፕሮግራሙም ዋንጫው የሚያቆራርጣቸውን የአለማችንን ከተሞች አጠር አርጎ በሚያስቃኝ ፊልም የጀመረ ሲሆን በመቀጠልም ዕንግዶቹ ንግግር አድርገውበታል።

በቅድሚያ ንግግር ያደረጉት ወ/ት ትዕግስት ጌቱ ኮካ ኮላ ዋንጫው ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ብዙ ጥረት እናደደረገ እና በሀገሪቷ ያለው የእግር ኳስ ፍቅርም ይህ እንዲሆን የነበረውን ትልቅ አስተዋፅዖ አስረድተው ዋንጫው በሚመጣበት ወቅት የሚኖረውን ፕሮግራም ዘርዝረዋል። በዚህም መሰረት የአለም ዋንጫ ቅድሜ የካቲት 17 ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ የታወቀ ሲሆን በቦሌ አለም ማቀፍ አየር ማረፊያ አቀባበል ከተደረገለት በኃላ በቀጥታ የሚያመራው ወደ ብሔራዊ ቤተመንግስቱ እንደሆነ ታውቋል። የቤተመንግስት ቆይታውን ካጠናቀቀ በኃላም ወደ ሒልተን ሆቴል የሚወሰድ ሲሆን በሆቴሉም ጋዜጣዊ መግለጫ ፣ የራት ግብዣ እና የፎቶ ፕሮግራም እንደሚኖር ተጠቁሟል። በቀጣዩ ዕለተ ዕሁድ የካቲት 18 ደግሞ ዋንጫው በጊዮን ሆቴል ለጉብኝት ቀርቦ ለህብረተሰቡ ክፍት እንደሚደረግ ተገልጿል።

በመቀጠል ንግግር ያደረጉት አቶ ጁነዲን ባሻህም አጋጣሚው የፈጠረባቸውን ደስታ የገለፁ ሲሆን በኮፓ ኮካ ኮላ ውድድር እና በሌሎችም ስራዎች ላይ ከፌዴሬሽኑ ጋር በቅርበት የሚሰራውን የኮካ ኮላ ካምፓኒ ዋንጫው ወደ ከተማችን እንዲመጣ ላበረከተው አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል። ፕሬዘዳንቱ የአለም ዋንጫ ከዋንጫነት ባለፈ በየሀገራቱ ያሉ የእግር ኳስ ባለ ድርሻ አካላትን የሚወክል በመሆኑ ስላለው ትልቅ ትርጉምም በሰፊው አስረድተዋል። አያይዘውም በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው ቻን 2020 ከዘንድሮው አዘጋጅ ሀገር ሞሮኮ የተረከቡትን የውድድሩን አርማ በስፍራው ለነበሩ አካላት ያቀረቡ ሲሆን ውድድሩን በብቃት ለማስተናገድ በሁሉም ዘርፎች ሊሰሩ የሚገቡ ስራዎች ካሁኑ መጀመር እንዳለባቸው አሳስበዋል። 

በመጨረሻም የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትር ተወካይ የሆኑት አቶ መንግስቱ ሳህሌ የአለም ዋንጫው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣቱ የተሰማቸውን ደስታ በመግለፅ ለኮካኮላ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ሕብረተሰቡ ዋንጫው በከተማዋ በሚቆይባቸው ሁለት ቀናት ልዩ ጥበቃ እና ከለላ እንዲያደርግለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *