​ወልዲያ ስድስት ተጫዋቾች ቡድኑን በፍጥነት እንዲቀላቀሉ አሳስቧል

በሳምንቱ መጀመርያ ወደ መደበኛ ልምምድ የተመለሰው ወልዲያ ስፖርት ክለብ ከቡድኑ ጋር እስካሁን ያልተቀላቀሉ ተጫዋቾች በፍጥነት ቡድኑን እንዲቀላለቀሉ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን ይህ ተግባራዊ የማይሆን ከሆነ ቀጣይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።

ከውድድር አመቱ ጅማሮ አንስቶ በተለያዩ ምክንያቶች ከውዝግቦች ያልራቀው ወልዲያ በቅርቡ በአካባቢው በተፈጠረው ወቅታዊ አለመረጋጋት የተነሳ ለአስራ አምስት ቀናት ያህል ቡድኑን በጊዜያዊነት መበተኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። በአሁኑ ወቅት ከተማዋ በመረጋጋቷ እንዲሁም በቡድኑ አባላት እና አመራሮች መካከል በተፈጠረው መግባባት የቡድኑ አብዛኛው አባላት ወደ ወልዲያ ባለፈው ሰኞ በማምራት ልምምድ ከረቡዕ አንስቶ እየሰሩ ይገኛሉ። የከተማዋ ነዋሪዎች እና ደጋፊዎች እንዲሁም የክለቡ አመራሮች ደማቅ አቀባበል ሲያደርጉላቸው በትናትናው ዕለት የእንኳን ደህና መጣቹ ግብዣ እንደተደረገላቸው ታውቋል። በቀጣይ ላሉበት ተስተካካይ ጨዋታዎችም በጥሩ መንፈስ ተረጋግቶ ዝግጅቱን እያከናወነ ይገኛል።

ሶከር ኢትዮዽያ ከክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ገረመው ባገኘችው መረጃ ስድስት ተጫዋቾች እስካሁን ቡድኑን መቀላቀል አልቻሉም። ” ቡድኑ በጥሩ መንፈስ ሆኖ ስራውን እየሰራ ይገኛል። ሆኖም ፍፁም ገብረማርያም ፣ ያሬድ ብርሃኑ ፣ ታደለ ምህረቴ ፣ ምንያህል ተሾመ ፣ አማረ በቀለ እና ኤደም ኮድዞ እስካሁን ቡድኑን አልተቀላቀሉም።  ፍፁም ስጋት እንዳለበት የገለፀ ቢሆንም አሁን ሁሉም ነገር እንደተስተካከለ መመለስ እንደሚችል ገልፀንለት አልመጣም ፤ አማረ በቀለ በቅጣት ላይ የሚገኝ በመሆኑ የሚጨርሰው ጉዳይ እንዳለበት በቅርቡም እንደሚመጣ ገልፆልን ሳይገባ ቀርቷል ፤ የተቀሩት አራት ተጨዋቾች ግን ምክንያታቸውን አላሳወቁም። ወልዲያ ከዚህ በኋላ በተከታታይ ቀናት ተደራራቢ ጨዋታ የሚጠብቀው በመሆኑ ከቡድኑ ጋር እንዲቀላቀሉ ለሚመለከታቸው አካላት በግልባጭ ደብዳቤ አሳውቀናል። በፍጥነት ስራቸውን የማይጀምሩ ከሆነ ግን ወደ ቀጣይ እርምጃ ክለቡ የሚያመራ ይሆናል ” ብለዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የተጫዋቾቹን አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት ያልተሳካ ሲሆን ምላሻቸውን በቀጣዮቹ ቀናት ይዘን ለመመለስ እንጥራለን።

ወልዲያ በተለያዩ ጊዜያት ያላደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች (ከኤሌክትሪክ ፣ መከላከያ እና ደደቢት) እንዲሁም በ15ኛው ሳምንት ከወላይታ ድቻ ጋር ሊያደርገው የነበረውና በድቻ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ የተሸጋገረውን ጨዋታ ፌዴሬሽኑ ወደፊት በሚገልፃቸው ቀናት የሚያደርግ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *