የፊፋ ደብዳቤ የአስመራጭ ኮሚቴውን ክፍፍል አጉልቷል

የዓለምአቀፉ እግርኳስ የበላይ አስተዳዳሪ አካል የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን የፕሬዝደንታዊ እና ስራ አስፈፃሚ ምርጫን በበላይነት እንዲመራ ለተመረጠው የአስመራጭ ኮሚቴ ጥር 23 የላከው ደብዳቤ አንዳንድ የኮሚቴውን አባላት አላስደሰተም፡፡

ምርጫው ሶስት ግዜያት ተላልፎ የካቲት 24 ሰመራ ከተማ እንደሚካሄድ ሲገለፅ ከመቆየቱም በላይ የፊፋ እና ካፍ ታዛቢዎች በተገኙበት እንደሚካሄድ ተነግሮ ነበር፡፡ ፊፋ ከዚህ ቀደም በታህሳስ 30 በላከው ደብዳቤ የአስመራጭ ኮሚቴውን ሰብሳቢ የአቶ ዘሪሁን መኮንን ስጋት እንደሚጋራ ገልፆ ምርጫው ያሉበትን የአሰራር ክፍተቶችን አሟልቶ አንዲደረግ እና ይህም ከአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) መጠናቀቅ በኃላ እንዲደረግ ባቀረበው ሃሳብ መሰረት ምርጫው ለሶስተኛ ግዜ ተራዝሞ ነበር፡፡ ሰኔጋላዊቷ የፊፋ ዋና ፀሃፊ ፋትማ ሳሞራ በፈረመችበት ደብዳቤ ላይ የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን የፊፋ የምርጫ ኮድ አንቀፆች የሚሽር ሆኖ መገኘቱን መግለፃቸውን አስታውሶ የጠቅላላ ጉባኤው የፊፋ የምርጫ ኮድ አንደመመሪያ ሲጠቀምበት እንደነበረ መረዳቱን ይገልፃል፡፡ እንዲሁም ለቀጣይ ምርጫዎች ፌድሬሽኑ የእራሱን የምርጫ ኮድ እንዲኖረው አስገንዝቦ ለዚህም ፊፋ አስፈላጊውን ክትትል እና ድጋፍ እንደሚያደርግ ደብዳቤው ጠቁሟል፡፡ ለአሁኑ ምርጫ ግን የፌድሬሽኑ ደንብ እና የዓለምአቀፉን የምርጫ ኮድ እንዲከተል ደብዳቤ አስገንዝቧል፡፡
የደብዳቤው ዋና ጭብጥ ተከሰቱ የተባሉትን የአሰራር ክፍተቶች እንዲስተካከሉ እና እንዲታረሙ በር አልከፈተም በሚል የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን ለፊፋ ደብዳቤ መላካቸውን ምንጮቻችን ነግረውናል፡፡

ከአሰራር ክፍተቶቹ መካከልም በአስመራጭ ኮሚቴው እና የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴው አባላት ለሁለት ተከታታይ ምርጫዎች ላይ በተጠቀሱት ኮሚቴዎች ውስጥ መስራት አይችሉም የሚለው የምርጫ ኮድ አንቀፅን በሻረ መልኩ አንዳንድ አባላት ለሁለተኛ ተከታታይ ግዜ በኮሚቴው ውስጠ መገኘታቸውን እና ሌሎች የአሰራር ክፍተቶችን ለማረም ፊፋ በደብዳቤው አላስቀመጠም በሚል ነው አቶ ዘሪሁን ቅሬታቸውን ያሰሙት፡፡ እንዲሁም የህግ ክፍተቶቹ እየታዩ ፊፋ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ አለመቻሉ የአስተዳደር ብቃቱንም አጠያያቂ እንደሚያደረግ አቶ ዘሪሁን በደብዳቤያቸው መግለፃቸውን ምንጮቻችን አስተውቀዋል፡፡ በቅሬታቸውም እንነዚህ የአሰራር ግድፈቶች የማይስተካከሉ ከሆነ እራሳቸውን ከአስመራጭ ኮሚቴ ሰብሳቢ በገዛ ፍቃዳቸውን እንደሚያነሱ ተነግሯል፡፡

አቶ ዘሪሁን ለፊፋ በላኩት ደብዳቤ ላይ የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት ማወቅ አለመቻላቸው ነገሩን ይበልጥ እንዲካረር አድርጎታል፡፡ አቶ ዘሪሁን እና አንዳንድ የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት መሃልም በዚሁ ምክንያት አለመግባባት መፈጠሩን ሰምተናል፡፡ ፌድሬሽኑ ጥር 23 ፊፋ የላከውን ደብዳቤ ይፋ ሳያደርግ ለ9 ቀናት የቆየ ሲሆን በየካቲት 1 ነበር ለአስመራጭ ኮሚቴው አባላት ይህ ደብዳቤ ይፋ የተደረገው፡፡ ለዚህም ምክንያት ተብሎ የቀረበው የፌድሬሽኑ አንዳንድ ሃላፊዎች በቻን እና የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ ምክንያት ሃገር ውስጥ ባለመገኘታቸውን ነው ተብሏል፡፡

በቀጣይ ስለአቶ ዘሪሁን ለፊፋ የላኩት ደብዳቤ ይዘት እና ሌሎች የሚወጡ አዳዲስ መረጃዎችን በነገው እለት ይዘን እንመለሳለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *