​ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ሀዋሳ ከተማ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ተስተካካይ ጨዋታዎች ሰሞኑን በመደረግ ላይ ሲሆኑ ዛሬም ኢትዮጵያ ቡና ሀዋሳ ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ይጠበቃል። ይህን ጨዋታም እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በሊጉ በእርስ በእርስ ግንኙነታቸው ጥሩ ፉክክር ከሚያደርጉ ክለቦች መሀከል የዛሬዎቹ ተጋጣሚዎች ኢትዮጽያ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ ተጠቃሾች ናቸው። ግቦች የማያጡት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከ1996 ጀምሮ በተገናኙባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ቢያንስ አንድ ጎል ሲያስመለክተን ቆይቷል። የኢትዮጽያ ፕሪሚየር ሊግ በ1990 በአዲስ ፎርማት ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን ድረስ እየተካፈሉ ከሚገኙ ሶስት ክለቦች መሀከል የሆኑት ኢትዮጵያ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ የእርስ በእርስ ውጤታቸውም በመሀላቸው ያለውን የፉክክር ሚዛናዊነት የሚያሳይ ነው። ባለፉት 19 የውድድር አመታት 38 ጊዜ ሲገናኙ ሁለቱም እኩል 12 ጊዜ አሸናፊ ለመሆን ችለዋል። ቀሪዎቹ 14 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ። በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ቅድሚያውን የወሰደው ኢትዮጵያ ቡና እስካሁን 45 ጊዜ ኳስ እና መረብን ሲያገናኝ ሀዋሳ ከተማም ሶስት የፎርፌ ግቦችን ጨምሮ 41 ግቦችን ማስመዝገብ ችሏል።

የመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታውን የሚያደርገው ኢትዮጵያ ቡና እንደአብዛኛው ጊዜ ሁሉ ቀስ በቀስ ወደ ጥሩ የውድድር መንፈስ እየተመለሰ ይገኛል። ቡድኑ እስካሁን ከሰበሰባቸው 19 ነጥቦች መሀከልም ሰባቱን ማሳካት የቻለው ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ነው። ከተደጋጋሚ የአሰልጣኝ ለውጦች እና አለመረጋጋቶች በኃላም ቡናማዎቹ በፈረንሳዊው አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜዝ ስር ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎችን ያለሽንፈት ማጠናቀቅ የቻሉት። ደብዛዛ የውድድር አመት እያሳለፈ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ ደግሞ የውጤት ማሽቆልቆሉ አሁንም እንደቀጠለ ነው። ቡድኑ ለመጨረሻ ጊዜ ድሬደዋ ከተማን ካሸነፈበት የሰባተኛ ሳምንት ጨዋታ በኃላ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ሁለቴ ሽንፈት ሲገጥመው ቀሪዎቹን በአቻ ውጤት ጨርሷል። ሁለቱ ሽንፈቶች የተመዘገቡትም ከሜዳ ውጪ በተደረጉ ጨዋታዎች ነው። እስካሁንም ቡድኑ ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች በሁለቱ ብቻ ነው ነጥብ የተጋራው። በፌደራል ዳኛ ሰለሞን ገ/ሚኢካኤል የመሀል ዳኝነት በሚደረገው የዛሬው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ነጥቡን 22 በማድረስ የመጀመሪያውን ዙር እስከ ስድስት ባለው ደረጃ ላይ ሆኖ ለማጠናቀቅ ሀዋሳ ከተማ ደግሞ የመጀመሪያውን የሜዳ ውጪ ድል በማሳካት ከወራጅ ቀጠናው በደንብ ለመራቅ በማሸነፍ ላይ ብቻ ተመስርተው በሙሉ የማጥቃት ሀይላቸው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል።  

የኢትዮጵያ ቡናዎቹ አክሊሉ አያናው ፣ አለማየው ሙለታ እና አስቻለው ግርማ ከጉዳት ያላገገሙ ሲሆን አማካዩ አማኑኤል ዮሀንስም በሀዘን ምክንያት ለዛሬው ጨዋታ እንደማይደርስ ሰምተናል። ላውረንስ ላርቴ እና ዳንኤል ደርቤ ከጉዳት በተመለሱለት ሀዋሳ ከተማ በኩል ሳዲቅ ሴቾ ፣ ያቡን ዊልያም እና ተክለማርያም ሻንቆ አሁንም ጉዳት ላይ ሲገኙ ፍሬው ሰለሞንም በቅጣት ከዛሬው ጨዋታ ውጪ ነው። 


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


ኢትዮጵያ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ ተመሳሳይ የጨዋታ አቀራረብ እንዳላቸው ይታወቃል። ሁለቱም ኳስን ለረዥም ጊዜ ተቆጣጥረው በተጋጣሚ የተከላካይ መስመር ጀርባ ለመግባት ቀዳዳዎችን በመፈለግ ሰፊ ጊዜን የሚወስዱ ሲሆን ይህ አቀራረባቸው የተለወጠበት አጋጣሚም አልነበረም። በዛሬውም ጨዋታ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ለመውሰድ እንደሚፋለሙ ይጠበቃል። ሆኖም ግን ሁለቱም ቡድኖች ከሚያገኙት የኳስ ቁጥጥር የበላይነት አንፃር ከግቡ ቅርብ ርቀት ላይ በመገኘት የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን በመፍጠርም ሆነ የተገኙትን ዕድሎች በአግባቡ በመጨረሱ በኩል ድክመት ይታይባቸዋል። በዚህ ረገድ የተወሰነ መሻሻል ያሳየው ኢትዮጵያ ቡና ተከታታይ ድል ባስመዘገበባቸው የድሬደዋ እና ፋሲል ከተማ ጨዋታዎች አምስት ግቦችን ማስቆጠር ቢችልም ይህ ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ተቀርፏል ለማለት ግን አያስደፍርም። ባለፉት አምስት ጨዋታዎቹ በአንድ አጋጣሚ ብቻ ግብ ማስቆጠር የቻለው ሀዋሳ ከተማ ደግሞ በዚህ ረገድ የከፋ ችግር ይታይበታል። ቡድኑ የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎቹ በተደጋጋሚ ጉዳት እና ቅጣት ከአሰላለፍ ውጪ የሚሆኑበት አጋጣሚ ፊት ላይ ሊኖረው የሚገባውን ውህድት እያሳጣው ይገኛል። ከአማካይ ክፍል ተሰላፊዎችም በሚፈለገው መጠን ግቦችን አለማግኘቱ እና ደካማ የሚባለው የቆመ ኳስ አጠቃቀሙ በተጨማሪ መንገዶች ግቦችን እንዳያገኝ ምክንያት ሆነውታል። በዛሬው ጨዋታ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመግባት ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ ዕድሎችን በመጠቀም በኩል የተሻለ የሚሆነው ቡድን ተጠቃሚ መሆኑ የማይቀር ቢሆንም ጊዜ እና ቦታቸውን የጠበቁ ስኬታማ የኳስ ቅብብሎችን በማድረግ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን የሚወስደው ቡድን ዕድሎችን የመፍጠር አጋጣሚውም የሰፋ ይሆናል። በዚህ ረገድ በጨዋታው አማካይ ክፍል ላይ የሚደረገው ፍልሚያ ተጠባቂ ነው። የቡድኖቹ የመስመር ተከላካዮች እና የመስመር አጥቂዎችም በተመጠነ ርቀት ለአማካይ ክፍላቸው በመቅረብ የኳስ ፍሰቱ ስኬታማ እንዲሆን የሚያደርጉት ጥረት ወሳኝ እንደሚሆን ይጠበቃል። ይህ እንዲሆንም ከኬስ ውጪ በሚኖራቸው እንቅስቃሴ የቅብብል መስመሮችን ለመፍጠር በብምታ አያያዛቸው አንዳቸው ከሌላኛቸው ተሽለው እንዲገኙ ያስገድዳቸዋል። 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *