​“ ወላይታ ድቻ ከሜዳ ውጪ ባስቆጠረው ግብ ምክንያት የበላይ ነው” አብደልጋኒ ምሶማ

በቶታል ካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ቅደመ ማጣሪያ ጨዋታ ወላይታ ድቻ የዛንዚባሩን ዚማሞቶን በሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ረቡዕ ያስተናግዳል፡፡ ከአስር ቀናት በፊት ሁለቱ ቡድኖች ዛንዚባር ሲቲ በሚገኘው አማን ስታዲየም ባደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ መለያየታቸው ይታወቃል፡፡ 

በኮንፌድሬሽን ዋንጫ የመጀመሪያ ተሳትፎ እያደረገ የሚገኘው ዚማሞቶ በሜዳው በተቆጠረበት ግብ ምክንያት ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ አጣብቂኝ ውስጥ ይገኛል፡፡ በዛንዚባር እግርኳስ የካበተ ልምድ ያላቸው አሰልጣኝ አብደልጋኒ ምሶማ ኬንያ በ2017 ባስተናገደችው የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ እስከፍፃሜ የተጓዘውን የዛንዚባር ብሄራዊ ቡድን የልምምድ እቅድን በማውጣት ቁልፍ ሚናን ተውጥተዋል፡፡

ለሶስተኛ ግዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ምሶማ ዛንዚባርን ይዘው አሩሻ ላይ ኢትዮጵያን 3-1 የረቱ ሲሆን ዚማሞቶን ወደ አንደኛው ዙር የማሳለፍ ፈተናም ይጠብቃቸዋል። አሰልጣኙ ስለዚማሞቶ የማለፍ እድል እና ስለጨዋታው ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ስለጨዋታው

በመጀመሪያው ጨዋታ እኛ ከወላይታ ድቻ በላይ ነበርን፡፡ አራት የሚሆኑ የግብ እድሎችን አምክነናል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ አውቀው የመከላከልን አጨዋወት ተግብረዋል፡፡ ለማጥቃት አልደፈሩም ፤ አንድ ግዜ ብቻ ነው የሞከሩት፡፡ ይህ የእነሱ ታክቲክ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ማጥቃት እንደሚችሉ አውቃለው። ምክንያቱም ጥሩ ቡድን ናቸው፡፡ በቴክኒኩ የላቁ እና የማቀበል ስኬታቸው ጥሩ የሆኑ ተጫዋቾች ይዘዋል፡፡ ከባድ ጨዋታ እንደሚሆን ተስፋ አደርገዋል፡፡

ራሳችንን ለመከላከል ነው እዚህ የተገኘነው፡፡ ቢሆንም ከሜዳ ውጪ ባስቆጠረው ግብ ወላይታ ድቻ የበላይ ነው፡፡ በተቻለ መጠን መስዋትነት ከፍለን ግብ ማስቆጠር አለብን፡፡ ይህ ዋነኛ አላማችን ነው፡፡

ወደ ቀጣይ ዙር የማለፍ እድል

ይህ አላማችን ነው፡፡ ትንሽ አስቸጋሪ እንደሚሆን እናውቃለን፡፡ ምክንያቱም ዛንዚባር ላይ እድሎቻችን አምክነናል፡፡ ወላይታ ድቻ ዛንዚባር ላይ ደካማ ነበር፡፡ ዛንዚባር በጣም ሞቃታማ ነው፡፡ ወዲያው ነው የሚያልብህ፡፡ በደንብ ሊጫወቱ አልቻሉም፡፡ እዚህ በጨዋታ ሊጨርሱን እንደሚሞክሩ እንረዳለን፡፡ ለዚህም ራሳችንን እያዘጋጀን ነው፡፡

እየተበላሽ ስለመጣው የሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ሜዳ

ይህ የመጫወቻ ሜዳ አዲስ ይመስላል፡፡ ሆኖም ሜዳው ጥሩ አይደለም፡፡ በጨዋታ ወቅት ጥሩ እንደሚሆን እገምታለው፡፡ እየተጠገነ ያለሜዳ ይመስላል፡፡ ግን ጥሩ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *