​” ጨዋታው ገና እንዳላለቀ ከተጫዋቾቼ ጋር ተነጋግረናል ” ዘነበ ፍሰሀ

በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው ወላይታ ድቻ በቅድመ ማጣርያ የመልስ ጨዋታ የዛንዚባሩ ዚማሞቶን ነገ 10:00 ላይ በሀዋሳ ስታድየም ያስተናግዳል። የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሀ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ስለ ነገው ጨዋታ አስተያየታቸወረን ሰጥተዋል።

ለመልሱ ጨዋታ ዝግጅታችሁ ምን ይመስላል? ነገስ ምን እንጠብቅ ?

የመጀመሪያውን ጨዋታ ከሜዳችን ውጭ እንደማድረጋችን የዚማሞቶን ቡድን ከሞላ ጎደል በሜዳ ላይ ያደረጉትን እንቅስቃሴ አይተናል። የነሱ ጠንካራ ጎን ምን እንደሆነም ተመልክተናል።  በዛ መልኩ በሜዳችን በምናደርገው ጨዋታ ኳሱን ተቆጣጥረን በመጫወት እና ባለፈው የነበረብንን ስህተት በማረም አሸንፈን ለመውጣት በደንብ ተዘጋጅተናል።

ስለ ተጋጣሚያችሁ ያላችሁ አስተያየት ምንድነው? የዚማሞቶ ጥንካሬን በሚገባ አውቃችዋል? 

አብዛኛው የነሱ ጠዋታ ከመስመር የሚመጣ ኳስ ነው። ረጃጅም ኳስ ነው የሚጠቀሙት። ተጫዋቾቻችን በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ትኩረት እንዲሰጡ ከተጫዋቾቼ ጋር ተነጋግረናል። በተነጋገርነው መሠረት ሜዳ ላይ የምናደርገው እንቅስቃሴ ጥሩ ነው። ለውጥ እያየን ነው ፤ ያንን እንቅስቃሴም በሚገባ ይተገብራሉ ብዬ ሙሉ እምነት አለኝ። ጨዋታው ወሳኝ ነው ፤ አንድ ዘጠና ደቂቃ ነው የቀረን። በዚህ ዘጠና ደቂቃ ውስጥ አሸንፈን የምንወጣበትን መንገድ ብቻ ነው የምንፈልገው። እንቅስቃሴያችንንም በማጥቃት ላይ ትኩረት አድርገን ነው የምንገባው። በልጠን ተጫውተን አሸንፈናቸው እንደምንወጣ እርግጠኛ ነኝ፡፡

ከሜዳችሁ ውጭ አቻ እንደመለያየታችሁ እና ከክለቡ ደረጃ አንፃር ለጨዋታው የሰጣችሁት ትኩረት ምን ይመስላል? ለመሰል ጨዋታዎች የሚሰጡ ዝቅተኛ ትኩረቶች ዋጋ እንዳያስከፍላችሁ ምንያህል ተዘጋጅታችኋል?

ያልከው ነገር ትክክል ነው። እኛ አካባቢ ይሄ ሁልጊዜ ያለ ችግር ነው። ከሜዳ ውጭ ተጫውተን እንደመምጣታችን ቅድሚያ የያዝነው ውጤት ብዙ ጊዜ ያዘናጋናል። በጨዋታው ገና ብዙ ነገር ይቀረናል ፤ እኛ እንዳስቆጠርነው ሁሉ እነሱም ሊያስቆጥሩ ይችላሉ። ስለዚህ ጨዋታው እንዳላለቀ ለተጫዋቾቻችን ነግረናል። ይልቁንም በሜዳችን እንደመጫወታችን ጫና እንደሚጠብቀን ነው የተነጋገርነው። እያንዳንዱን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ትኩረት ሰጥተን ለመጫወት ስራ ሰርተናል።

የተጋጣሚያችሁ ክለብ አሰልጣኝ በጥንቃቄ እንደሚጫወቱ እና በመከላከል ላይ ተመስርተው ውጤት ይዘው ለመውጣት እንደሚገቡ ገልፀዋል…  

እነሱም ለማሸነፍ ነው የሚመጡት። ይሄ ውድድር እንደመሆኑ ማንም ቡድን የሚመጣው ለማሸነፍ ነው። እኛም የነሱን ጥቃት ለመመከት ሜዳ ላይ የሚፈጠሩትን በማየት እኛም በማንበብ እዛው ታክቲካችንን የምንቀይርበት ስራ ሰርተናል።

ክለቡን ከተረከቡ በኋላ ክለቡ በመልካም መንገድ እየተጓዘ የሚገኝበት ምስጢር ምንድነው ?

ይህ ምንም የተለየ ሚስጥር የለውም። ተጫዋቾቹ ያላቸውን አቅም አውጥተው እንዲጫወቱ ነው ያደረኩት። መጫወት እንደሚችሉ ራሳቸውንም እንዲያሳምኑ እና እችላለሁ የሚል ነገር በውስጣቸው እንዲኖር በእንቅስቃሴም የተቻላቸውን ሁሉ በተነሳሽነት እንዲያደርጉ በማድረጌ ነው ለውጥ የመጣው እንጂ ሌላ የተለየ ነገር ግን የለውም።

ወላይታ ድቻ በርካታ ደጋፊዎች ያሉት ክለብ ነው። በነገው ጨዋታ ዙርያ ስለ ደጋፊዎቹ ምን ይላሉ?

ለደጋፊዎቹ የምለው እኛ ያለንን ሁሉ አውጥተን ለመጫወት እና ህዝቡን ለማስደሰት ፣ ደጋፊዎቻችንንም ሆነ የኢትዮጵያን ስም ለማስጠራት ቆርጠን ነው የተነሳነው። ደጋፊዎቻችን በነገው እለት ዘጠና ደቂቃውን ሙሉ ከጎናችን ሆነው እንዲያበረታቱን ነው መልዕክቴን የማስተላልፈው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *