አዳማ ከነማ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ተመልሷል

አዳማ ከነማ እግርኳስ ክለብ ዛሬ በተደረገው የብሄራዊ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ ሱሉልታ ከነማን በመለያ ምቶች አሸንፎ ወደ ፍፃሜው ሲያልፍ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማለፉንም አረጋግጧል፡፡

በአራት ሰአት በተካሄደው ጨዋታ መደበኛውን 90 ደቂቃ በ 1-1 አቻ ውጤት ያጠናቀቁ ሲሆን ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዘው አዳማ ከነማ በ11ኛው ደቂቃ በቢንያም የወንድወሰን አማካኝነት ባስቆጠረው ግብ ነው፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ በ72ኛው ደቂቃ ሱሉልታዎች በታከለ አለማየው አማካኝነት ግብ አስቆጥረው አቻ ሆነው ጨዋታው በ1-1 አቻ ውጤት መደበኛው 90 ደቂቃ ተጠናቋል፡፡

አሸናፊውን ለመለየት በቀጥታ ወደ መለያ ምቶች አምርተዋል፡፡ በመለያ ፍፁም ቅጣት ምቱ አዳማ ከነማዎች በአብዱልከሪም በለጠ ፣ አብዱልከሪም አባፎጊ እና በረከት አዲሱ አማካኝነት በተከታታይ 3 ግቦች ሲያስቆጥሩ ሱሉልታ ከነማዎች በተከታታይ 3 ምቶችን ስተው ጨዋታው በአዳማ ከነማ 4-1 አጠቃ፤ይ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በ2005 የውድድር ዘመን ከፕሪሚየር ሊጉ የወረደው አዳማ ከነማ በአንደኛ አመቱ ወደ ፕሪሚር ሊጉ ተመልሷል፡፡ በርካታ ክለቦች በወረዱበት አመት ለመመለስ ከሚቸገሩበት ብሄራዊ ሊግ አዳማ ከነማ መመለሱ አስደናቂ ነው፡፡

ከዚህ በፊት በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ በወረዱ በአመታቸው የተመለሱት 3 ክለቦች ብቻ ናቸው፡፡ አዳማ ከነማ ከኮምቦልቻ ጨጨ ፣ ጉና ንግድ እና ወንጂ ስኳር በመቀጠል 4 ክለብ ሆኗል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *