ኢትዮጵያዊው አብርሃም መብራቱ የመንን ለእስያ ዋንጫ አሳልፏል

በ2019 የተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች ለምታስተናግደው የእስያ ዋንጫ ለማለፍ የሚደረጉ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ሲጠናቀቁ ከምድብ 6 የመን በታሪኳ ለመጀመሪያ ግዜ ማለፏን አረጋግጣለች፡፡ የመን የፊሊፒንስ ታጃኪስታንን 2-1 ማሸነፍ ተከትሎ ነው ማለፍ የቻለችው፡፡ አሰልጣኝ ኢትዮጵያዊው አብርሃም መብራህቱም ብሄራዊ ቡድኑን እየመራ ለዚህ ክብር አብቅቷል፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ ከሃገሩ ውጪ እንደዚህ ያለ ስኬት ሲያስመዘግብ በቅርብ ግዜያት ይህ ለመጀመሪያ ግዜ ነው፡፡

የመን የካታር መዲና ዶሃ ላይ ኔፓልን አስተናግዳ 2-1 በማሸነፍ ፊሊፒንስን ተከትሎ ወደ እስያ ዋንጫ አምርታለች፡፡ በሱሂም ቤን ሃማድ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ለየመን ፈታኝ ቢመስልም አብዱልዋሲ አል ማታሪ በ24 እና 84ኛው ደቂቃ ባስቆጠራቸው ግቦች ኔፓልን መርታት ችላለች፡፡ ድሉን ተከትሎ የመን በ10 ነጥብ ምድቡን በሁለተኛነት ያጠናቀቀች ሲሆን ባደረጋቻቸው 6 ጨዋታዎች በሁለት አሸነፋ በአራት ጨዋታ ነጥብ ተጋርታለች፡፡

የመን በእርስ በእርስ ጦርነት መታመስ እና የሌሎች ሃገራት የእጅ አዙር ግጭት መነሃሪያ ብትሆንም ብሄራዊ ቡድኑ በአሰልጣኝ አብርሃም እየተመራ ወደ እስያ ዋንጫ የሚወስደውን ትኬት ቆርጧል፡፡ አሰልጣኝ አብርሃም የካፍ ኢንስትራክተር ሲሆን ከ1980ዎቹ ጀምሮ የተለያዩ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ከማሰልጠኑ ባሻገር የየመን እግርኳስ ፌድሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር በመሆን አገልግሏል፡፡ የየመን እግርኳስ ከ1990ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ከኢትዮጵያዊያን ጋር የተቆራኘ ሲሆን እስከቅርብ አመታት ድረስም ኢትዮጵያዊያን አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች በሊጉ ቆይታን አድርገዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *