ሲዲ ኬታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተለያይቷል

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከማሊያዊው አጥቂ ሲዲ መሃመድ ኬታ ጋር መለያየቱን ዛሬ በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ አስታውቋል፡፡ ኬታ ፈረሰኞቹን በጥቅምት 2010 የተቀላቀለ ሲሆን በሚጠበቀው መልኩ ግልጋሎት ሳይሰጥ በክለቡ የነበረው ቆይታ አብቅቷል፡፡

ኬታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የነበረው የሁለት ዓመት ውል በስምምነት መፍረሱ ክለቡ ገልጿል፡፡ የፊት መስመር ተጫዋቹ በክለቡ የተወሰኑ ጨዋታዎች ላይ ተቀይሮ የተጫወተ ሲሆን በቆይታውም አንድ የሊግ ግብ አስቆጥሯል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በካፍ ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ በዩጋንዳው ኬሲሲኤ ተሸንፎ ከውድድር ውጪ ሲሆንም ወደ ካምፓላ ያልተጓዘ ሲሆን ክለቡ በእሱ ላይ የነበረው እምነትም ከተሸረሸረ መቆየቱን ያመላከተ ነበር፡፡

ኬታ አምና በማሊ ሊግ 1 በሚወዳደረው ሴንተር ሳሊፍ ኬታ የውድድር ዘመን ቆይታው 7 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ ቆይታው ይህንን ያህል የሚጠቀስ የረባ እንቅስቃሴ ሳያሳይ ከክለቡ ጋር ተለያይቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *