ወንድሜነህ ዘሪሁን ወደ ሲዳማ ቡና አምርቷል

ከቀናት በፊት ክለቡን በአግባቡ መጥቀም አልቻለም በሚል ከአርባምንጭ ከተማ ጋር በስምምነት የተለያየው የመሀል አማካዩ ወንድሜነህ ዘሪሁን ብዙም ሳይቆይ ለሲዳማ ቡና በአንድ አመት የውል ስምምነት ፈርሟል፡፡ 

ወንድሜነህ በበርካታ ክለቦች የተጫወተ ሲሆን በሙገር ፣ መከላከያ ፣ አዳማ ከተማ ፣ ኤሌክትሪክ እና ሀዋሳ ከተማ መጫወት የቻለ ተጫዋች ነው። ተጫዋቹ ከሁለት አመት በፊት አዳማ ከተማን ለቆ ወደ አርባምንጭ ከተማ ያመራ ሲሆን በዘንድሮው የውድድር ዘመን በተፈለገው ልክ ክለቡን በጉዳት ምክንያት ማገልገል ባለመቻሉ ምክንያት ቀሪ የስድስት ወራት ኮንትራት እያለው በስምምነት ተለያይቶ ነው አሁን ሲዳማ ቡናን የተቀላቀለው፡፡

በሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ጨዋታ በሜዳው በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈትን ያስተናገደው ሲዳማ ቡና በ17ኛ ሳምንት ወደ አርባምንጭ ተጉዞ አርባምንጭ ከተማን የሚገጥም ሲሆን ወንድሜነህ ለጨዋታ ዝግጁ የሚያደገውን የወረቀት ጉዳዮች በፍጥነት ከጨረሰ ሀሙስ የቀድሞ ክለቡን ሊገጥም ይችላል።

በተያያዘ ዜና ሲዳማ ቡና በከፍተኛ ዲሲፕሊን ግድፈት ምክንያት አሰናብቶት የነበረው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ዮሴፍ ዮሀንስን በመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መመለሱ ታውቋል። እንደምክንያት የቀረበውም ክለቡ ያለበት የአማካይ ተጫዋች እጥረት ነው ተብሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *