“የዚህ ታሪክ አንዱ አካል መሆን ያስደስታል” ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ

የመን በታሪኳ ለመጀመሪያ ግዜ በኢትዮጵያዊው አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ እየተመራች ለእስያ ዋንጫ አልፋለች፡፡ ማክሰኞ ምሽት ዶሃ ላይ ኔፓልን አስተናግዳ የመን 2-1 ማሸነፍ ችላለች፡፡ በእርስበእርስ ጦርነት የምትታመሰው ሃገር የተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች በ2019 ለምታስተናግደው የእስያ ዋንጫ ማለፍ የቻለችው ከምድብ 6 ፊሊፒንስን ተከትሎ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ነው፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ ከአሰልጣኝ አብረሃም ጋር ስለየመን የእስያ ዋንጫ ጉዞ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ አጠር ያለ ቆይታን አድርጓል፡፡

በመጀመሪያ እንኳን ደስ ያለህ! ምን ተሰማህ?

በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ አልፈን ለዚህ በመብቃታችን በጣም ነው የተደሰትኩት፡፡ የመን ለመጀመሪያ ግዜ ነው ለእስያ ዋንጫ ያለፈችው፡፡ እግዚአብሄርን አመሰግናለው!

የማጣሪያ ጉዞው ምን ይመስል ነበር?

ማጣሪያ የጀመርነው ከአመት በፊት ነው፡፡ በፈረንጆቹ መጋቢት 2016 ማልዲቭስን በቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ አሸንፈን ነው ወደ ምድብ የገባነው፡፡ ባደረግናቸው 6 ጨዋታው 2 አሸንፈን በ4 ጨዋታ አቻ ወጥተናል፡፡ ወደ እስያ ዋንጫ ከማለፋችን በተረፈ በማጣሪያው አንድ ጨዋታ ሳንሸነፍ ለዚህ መብቃታችን በጣም የተለየ ስሜት ይፈጥራል፡፡ የዚህ ታሪክ አንዱ አካል መሆኑም ያስደስታል፡፡

የመን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ይህ ስኬት በጣም ትልቅ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ የገጠሟችሁ ችግሮች ምንድናቸው እንዲሁም በምን ዓይነት ሁኔታ አለፋችሁት?

በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ነበሩ በማጣሪያ ጉዟችን ላይ፡፡ የየመን የውስጥ ሊግ ላለፉት 4 ዓመታት በጦርነቱ ምክንያት ባለመኖሩ ተጫዋቾችን ለብሄራዊ ቡድን ማግኘት እና ጨዋታዎችን በበቂ ሁኔታ ማድረግ አስቸጋሪ ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም የኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ስለነበርኩ አብዛኞቹ ተጫዋቾችን ከ23 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ነው የመረጥነው፡፡ የመረጥነው 40 ተጫዋቾች ይሆናሉ፡፡ እነዚህን ለአራት በመክፈል እና እርስ በእርስ በማጫወት 25 ብቁ የሆኑ ተጫዋቾችን ይዘናል፡፡ ተጫዋቾች ከሊግ ውድድር ስለራቁ ፊትነሳቸው ይቀንሳል፣ የስነ-ልቦናው ጫና፣ ስልጣና ላይም ያለው ጫና እና ሌሎች አስቸጋሪ ነገሮች ነበሩ፡፡

ከዚህ ቀደም በአረቡ አለም የሚገኙት ሊበያ በ2014 የቻን ዋንጫን አሸንፋለች፤ ኢራቅ በ2007 የእስያ ቻምፒየን ሆናለች እንዲሁም አሁን በያዝነው ዓመት ሶሪያ ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ተቃርባ ነበር፡፡ እነዚህ ሃገራ ከየመን ጋር አንድ የሚጋሩት ነገር አለ ይህም በችግር ውስጥ ሆነው ይህንን ማሳካታቸውን ነበር…..

ለእስያ ዋንጫ የመን ስታልፍ እንደጠቀስኩት ለመጀመሪያ ግዜ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የየመን ኦሎምፒክ ቡድን ለእስያ ውድድር (2013 ላይ) ሲያልፍ እኔ ነበርኩ አሰልጣኙ፡፡ የአሁን ከኦሎምፒኩ በኃላ የመጣ ሁለተኛው ታላቅ ድል ነው፡፡ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ያለች ሃገር አንደመሆኗ ተጫዋቾች ከሃገራቸው እና ቤተሰቦቻቸው ርቀዋል፡፡ የሜዳችን ላይ ጨዋታዎችን በሙሉ ያደረግነው ካታር ላይ ነው፡፡ ይህም በሜዳችን እና ደጋፊዎቻችን ፊት የመጫወት ሁኔታን አሳጥቶናል፡፡ በእንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ላይ ሆነን ነው ይህንን ትልቅ ድል ያሳካነው፡፡ ዛሬ መላው የመን በደስታ ተውጧል፡፡ ሁሉም ተጫዋቾቻችን የመጡት ከሁሉም የየመን አከባቢዎች ነው፡፡ ለየመን የደስታ ሳምንት ነው፡፡ ሁሉም የመናዊያን በእዚህ አስቻጋሪ ግዜ ደስተኛ በመሆናቸው ደስ ብሎኛል፡፡

ይህንን ስኬት ያሳካው አሰልጣኝ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነው…..

ሁሌም የምናገረው ነገር አለ፡፡ ‘Football is not nationality; it is personality’ ደስታው ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ለእኔ ብቻ አይደለም፡፡ በካታር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ማመስገን እፈልጋለው፡፡ ከየመናዊያን እኩል በስታዲየም በመገኘት ድጋፋቸው ሳይሰስቱ ሰጥተውናል፡፡ ሁሉም ጨዋታዎች ላይ መጥተው ደግፈውናል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ከጨዋታው በፊት እና በኃላ የመልካም ምኞታቸውን ለገለፁልኝ በሙሉ እጅግ አድርጌ ማመስገን እፈልጋለው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *