ሪፖርት | የወልዋሎ እና መቐለ ከተማ ጨዋታ ከመጀመርያው አጋማሽ መሻገር አልቻለም

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት አዲግራት ላይ የተካሄደው የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጨዋታ በደጋፊዎች ረብሻ ምክንያት ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሳይካሄድ ቀርቷል። 

በወልዋሎ መሪነት የተጠናቀቀው የመጀመርያው አጋማሽ በአመዛኙ በመሃል ሜዳ ላይ የተገደበ ፣ የሚቆራረጥ ቅብብል እና አሰልቺ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ቢታይበትም በሙከራዎች የታጀበ ነበር። በ7ኛው ደቂቃ ቢስማርክ ኦፖንግ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ዮሀንስ ሽኩር ባዳነበት የመጀመርያ ሙከራቸውን ያደረጉት መቐለዎች የተከላካይ መስመራቸውን ወደ ራሳቸው ግብ ክልል በማስጠጋት በራሳቸው የሜዳ ክልል ተገድበው በመንቀሳቀስ አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት በያሬድ እና አማኑኤል አማካኝነት አደጋ ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ወልዋሎ በአንፃሩ መቐለ ከተማዎች ከፊት ለፊታቸው በተዉት ሰፊ ክፍተት በመጠቀም የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወስዱም እንደወሰዱት ብልጫ የጠሩ የግብ እድሎች መፍጠር ኣልቻሉም። ይልቁንም ከሳጥን ውጭ በረጅሙ የሚሞከሩ እና ከቆሙ ኳሶች አደጋ ለመፈረጠር ሲሞክሩ ታይተዋል።

በ31ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር በኩል ፕሪንስ ያሻማው ቅጣት ምት ዋለልኝ ገጭቶ የመቐለ ተከላካዮች ተደርበው አውጥተውበታል። በዚህ ሙከራ ተነቃቅተው በጨዋታው ጫና የፈጠሩት ወልዋሎዎች በ30ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ተሰማ ከረጅም ርቀት የመታውን ኳስ ኦቮኖ እንደምንም ወደ ውጭ አውጥቶታል።  የመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ይበልጥ ጫና መፍጠር የቻሉት ወልዋሎዎች በ32ኛው ደቂቃ ላይም ጎል ማስቆጠር ችለዋል። ፕሪንስ በቀኝ መስመር በኩል ያሻማው ቅጣት ምት አሳሪ አልመሐዲ ገጭቶ ወልዋሎን መሪ ማድረግ ችለዋል። ከጎሉ በኋላ የጠራ የግብ እድል ያልታየ ሲሆን በወልዋሎ መሪነት የመጀመርያው አጋማሽ ተገባዷል።

ሁለቱ ክለቦች እረፍት በወጡበት ሰዓት ግጭት የተቀሰቀሰ ሲሆን በርካታ ቁጥር ያላቸው የሁለቱም ክለብ ደጋፊዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በተቃራኒ ደጋፊዎች መካከል ሰፊ ክፍተት አለመኖሩ እና በቃላት ምልልሶች ምክንያት የተጀመረው ረብሻ ወደ ከፍተኛ ሁከት ተሸጋግሮም ጨዋታውን እሰረከመቋረጥ አድርሶታል።  የሁለቱ ቡድኖችን ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደግ ተከትሎ በክልሉ በታየው ከፍተኛ መነቃቃት ምክንያት ከወትሮው በተሻለ ወደ ሜዳ መምጣት የጀመሩት ሴቶች፣ ህፃናት እና የእድሜ ባለፀጎች ላይም ጉዳት ደርሶባቸው ታይተዋል።

ሁከቱ ለ30 ደቂቃዎች ያህል ከቆየ በሜዳው ያለው ሁኔታ መረጋጋት የታየበት ቢሆንም ግርግሩ ከስታድየሙ ውጪ ቀጥሎ እንደነበር ታዝበናል። ይህን ተከትሎም የጨዋታው አመራሮች የሁለተኛው አጋማሽ እንዳይካሄድ ወስነው ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሳይካሄድ ቀርቷል። የተቋረጠው ጨዋታም መቼ እንደሚቀጥል አልታወቀም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *