ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ6 ጨዋታዎች በኃላ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል

የ17ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ቀን ውሎ መጨረሻ በነበረው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፋሲል ከተማን 3-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። በውጤቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሁለት ወራት በፊት የዛሬው ተጋጣሚው ፋሲል ከተማን ጎንደር ላይ ካሸነፈ በኃላ ያገኘው የመጀመሪያው የሊግ ድልም ሆኖ ተመዝግቧል።

ሁለቱም ቡድኖች በ16ኛው ሳምንት ካደረጓቸው ጨዋታዎች በርካታ ለውጦችን አድርገዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬደዋ ላይ ከነበረው ተከላካይ መስመሩ መሀሪ መናን ብቻ አስቀርቶ በጉዳት በሚመስል መልኩ አስቻለው ታመነን እና ሳላዲን ባርጌቾን በምንተስኖት አዳነ እና ደጉ ደበበ ጥምረት ለውጧል። የቀኝ መስመር ተከላካዩ አብዱልከሪም መሀመድም በፍሬዘር ካሳ ቦታ የተተካ ሲሆን ሌላው ለውጥ የተደረገው ደግሞ አማካይ ክፍል ላይ ታደለ መንገሻን በአዳነ ግርማ በመቀየር ነበር። በሁሉም የቡድን ክፍሎቻቸው ውስጥ አንድ አንድ ለውጥ ያደረጉት ፋሲል ከተማዎች መሀል ተከላካይ ቦታ ላይ ሰንደይ ሙቱኩን በከድር ኸይረዲን ፣ አማካይ ቦታ ላይ ሔኖክ ገምቴሳን በኤፍሬም አለሙ እንዲሁም በመስመር አጥቂነት ራምኬል ሎክን በኤርሚያስ ኃይሉ ቦታ ተክተዋል። እነዚህን ለውጦች ያድርጉ እንጂ ሁለቱም በ4-3-3 አሰላለፍ ነበር ጨዋታውን የጀመሩት። 

የመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ቀዝቃዛ ነበሩ። በነዚህ ጊዚያት ምንም ምከራ ያልተደረገ ቢሆንም ቅዱስ ጊዮርጊሶች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ነበራቸው። ጊዮርጊሶች ከፊት የፋሲልን የተከላካይ መስመር ለመጫን የሞከሩባቸውም አጋጣሚዎች ነበሩ። በአንፃሩ ፋሲሎች ኳስ በሚያገኙበት አጋጣሚ ወደ ፊት ለመሄድ ጥረት ቢያደርጉም ቅብብሎቻቸው ከመሀል ሜዳ እምብዛም ማለፍ የቻሉ አልነበሩም። ከጨዋታው መቀዛቀዝ ባለፈ  ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጥሩ ከሚባሉ ርቀቶች ላይ የቆመ ኳስ ዕድሎችን ቢያገኙም ወደ መጨረሻ ሙከራነት መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል። መጠነኛ ካፊያ ያስተናገደው ሜዳም የኃላ መስመር ተሰላፊዎችን ስህተት እንዲሰሩ ምክንያት ለመሆን የተቃረበባቸውን አጋጣሚዎችም ተመልክተናል።

16ኛው ደቂቃ ላይ ከፋሲል ከተማ ተከላካዮች ስህተት የተገኘውን ኳስ አብዱልከሪም ኒኪማ ከረጅም ርቀት ሞክሮ የግቡ አግዳሚ ሲያወጣበት ነበር ጨዋታው ነፍስ የዘራበት። ይበልጥ በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ ብዙ ሰዐት ማሳለፍ የጀመሩት ፈረሰኞቹ በታደለ መንገሻ መሪነት በተደጋጋሚ  እስከ ሳጥኑ መግቢያ ድረስ ቢጠጉም 19ኛው ደቂቃ ላይ በአቡበከር ሳኒ እንዲሁም 30ኛው ደቂቃ ላይ በበሀይሉ አሰፋ ያደረጓቸው ሙከራዎች ከሳጥን ውጪ የተገኙ ነበሩ። ከኃላ የሚጀምረው የኳስ ምስረታቸው ታደለ መንገሻ ጋር በሚደርስባቸው አጋጣሚዎች ከፊት ያለው የሶስትዮሽ ጥምረት ብዙም ወደ መሀል ሜዳ የማይጠጋውን የፋሲል የተከላካይ ክፍል የሚያስከፍት አልነበረም። ቡድኑ በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች አማራ ማሌን እና ታደለ መንገሻን በጉዳት ማጣቱን ተከትሎ የሚቸገር ቢመስልም የመጀመሪያውን አጋማሽ በመሪነት ለማጠናቀቅ ግን አልተሳነውም። በመጨረሻዎቹ የአጋማሹ ደቂቃዎች በሁለት አጋጣሚዎች በተጋጣሚያቸው ሳጥን ውስጥ ተበራክተው መገኘት ችለው የነበሩት ጊዮርጊሶች በፈጠሩት ጫና መሀሪ መና ከሳጥን ውጪ የመታውን ኳስ ሚኬል ሳማኬ አድኖ ሲተፋ በቦታው የነበረው አሜ መሀመድ ወደ ጎልነት ቀይሮት በክለቡ መለያ የመጀመሪያ ግቡን ማስቆጠር ችሏል። 

በመጀመሪያው አጋማሽ ይስሀቅ መኩሪያ እና ራምኬል ሎክ ከርቀት ካደረጓቸው ሙከራዎች ውጪ ሌላ ዕድል መፍጠር ያልቻሉት ፋሲል ከተማዎች የሚታወቁበትን ፈጣን የማጥቃት ሽግግር በአግባቡ መተግበር አልቻሉም። የቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ ክፍል ከለዐለም በራቀባቸው አጋጣሚዎች ጥቃት ለመፈፀም ዕድሎች የነበሯቸው ቢሆንም እነዚህን ኳሶች ከመሀል ሜዳ ለማስጀምር ሲሞክር በሚታየው ሔኖክ ገምቴሳ እና በፊት አጥቂዎቹ በተለይም አብዱርሀማን ሙባረክ መካከል የነበረው መናበብ ደካማ ነበር። ከዚህ ውጪ ፋሲሎች 36ኛው ደቂቃ አካባቢ በራሳቸው አጋማሽ ኳስ በማንሸራሸር ተጋጣሚያቸውን ለመሳብ እና ክፍተት ለማግኘት ያደረጉት ጥረትም ከተከላካይ መስመሩ ርቀው የሚታዩት አማካዮች ኳስን ለመቀበል ራሳቸውን ምቹ ባለማድረጋቸው ሊሳካ አልቻለም። 

ሁለተኛው አጋማሽ በጀመረ አስር ደቂቃዎች ውስጥ የተጨዋቾች ጉዳት ተራው ወደ ፋሲል ከተማ ዞሮ መሀመድ ናስር እና አብዱርሀማን ሙባረክ በኤርሚያስ ኃይሉ እና ኤፍሬም አለሙ ተቀይረው ገብተዋል። ከቅያሪዎቹ በኃላም ፋሲሎች አሰላለፋቸውን ወደ 4-2-3-1 በመቀየር ራምኬል ሎክን በብቸኛ የፊት አጥቂነት መጠቀም ጀምረዋል። ይህ መሆኑ እና በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አዳነ ግርማ በታደለ መንገሻ መተካቱን ተከትሎ የተጨዋቹ ለፊት መስመሩ የቀረበ ቦታ አያያዝ ለፋሲሎች በመጠኑ የተሻለ ሊባል የሚችል የመሀል ሜዳ ነፃነት ሰጥቷቸዋል። ሆኖም እንደመጀመሪያው ሁሉ ቡድኑ የሜዳውን አጋማሽ እንዳለፈ የሚሰራቸው የቅብብል ስህተቶች ፍሪያማ ሙከራዎችን እንዳያደርግ ምክንያት ሆነዋል። ከዚህ ይልቅ በረጅሙ ከሚጣሉ ኳሶች እንዲሁም የቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ መስመር ወደ መሀል ሲጠጋ በመስመሮች በኩል የተሰነዘሩ ጥቃቶች የተሻሉ ነበሩ ማለት ይቻላል። ከዚህ ውስጥ 71ኛው ደቂቃ ላይ ያስር ሙገርዋ በረጅሙ ወደ ጊዮርጊስ ሳጥን  ያሻገረውን ኳስ ኤርሚያስ ኃይሉ መቆጣጠር ሳይችል ቀረ እንጂ ሁኔታው ወደ ጥሩ ሙከራ መቀየር የሚችል ነበር። 79ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ቀኝ መስመር ባደላ መልሶ ማጥቃት ፋሲሎች በፈጠሩት አጋጣሚ ፍሊፕ ዳውዝ ይዞት የገባው ኳስ ግን በራሱ ግብ መሆን ባይችል እንኳን ለአፄዎቹ ሁለት ነገሮችን አሳክቷል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ሳጥን መግቢያ ላይ ፍሊፕን ኳስ ለማስጣል የሞከረው ደጉ ደበበ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ሲወጣ የተሰጠውን ቅጣት ምት ደግሞ አምሳሉ ጥላሁን በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከታደለ ቅያሪ በኃላ በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተው የመጀመሪያው የጨዋታ ዕቅዳቸው እንደማይቀጥል ምልክት መስጠት የጀመሩት ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር አቡበከር ሳኒ በግራ መስመር ከተከፈት መልሶ ማጥቃት ወደ ውስጥ በተጣለው ኳስ ነበር። ከዚህ በኃላም ምንም እንኳን ቡድኑ የጠሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ባይችልም መሀል ሜዳ ላይ ከፋሲል አማካዮች የሚነጠቁ ኳሶችን በፍጥነት ወደ መስመሮች በማውጣት የቀድሞውን መልኩን የያዘ በሚመሰል መልኩ ጥቃቶችን ለመፈፀም ሲሞክር ታይቷል። 76ኛው ደቂቃ ላይ ጊዮርጊሶች የቁጥር ብልጫን ይዘው በቀኝ መስመር ከተሰነዘሩት መልሶ ማጥቃት ከግቡ ቅርብ ርቀት ላይ አሜ መሀመድ ጥሩ ዕድል አግኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረበት አጋጣሚም በዚህ ስር የሚካተት ነበር። ሆኖም ይህ አካሄድ ፍሪያማነቱ የታየው ከአምሳሉ የቅጣት ምት ጎል በኃላ ነበር።  85ኛው ደቂቃ ላይ ከምንተስኖት ከተጣለለት ኳስ በግራ በኩል ሰብሮ የገባው አቡበከር ሳኒ በሰይድ ሁሴን በመጎተቱ ሰይድ የኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ሁለተኛ ቀይ ካርድ ሰለባ ሲሆን የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ደግሞ አዳነ ግርማ አስቆጥሮ ቡድኑን በድጋሚ መሪ ማድረግ ችሏል።

ከአዳነ ጎል በኃላ የተቀሩት ደቂቃዎች የጨዋታው ፍጥነት በእጅጉ የጨመረባቸው እና ሁለቱም ቡድኖች የተሻለ የሚባል ክፍተት ያገኙባቸው ነበሩ። በፋሲል በኩል ኤርሚያስ ኃይሉ ሳጥን ውስጥ ከተላከለት ረጅም ኳስ አግኝቶት የነበረው የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚም በዚህ ሰዐት የታየ ነበር። ሆኖም ተጨዋቹ ሙከራ ከማድረጉ በፊት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች ደርሰው አስጥለውታል። በተቃራኒው በጭማሪ ደቂቃዎች ፈረሰኞቹ በቀኝ መስመር ሰብረው የገቡበት መልሶ ማጥቃት ግን ወደ ግብነት የተቀየረ ነበር። ግብ አስቆጣሪውም አሜ መሀመድ ሆኗል። አሜ ሳጥን ውስጥ ኳስ እየገፋ በመግባት ሳማኬ ጋር ደርሶ ነበር የአመቱን ሁለተኛ ግቡን ማስቆጠር የቻለው። ጨዋታው በዚህ መልኩ በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-1 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ቡድኑ ከድሉ ባሻገር ሁለቱ ተጨዋቾቹ ከመጎዳታቸው ውጪ ናትናኤል ዘለቀ ከረጅም ጊዜ ጉዳት ተመልሶ ለ14 ደቂቃዎች መጫወት መቻሉ መልካም ዜና ሆኖለታል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ቫስ ፒንቶ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

የዛሬው ጨዋታ ለኛ የተለየ ነበር። ምክንያቱም ጥሩ ተጫውተን ማሸነፍ ያልቻልንባቸው ጨዋታዎች ነበሩ ፤ ድሬደዋ ላይ እንደነበረው። ዛሬም በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ የማግባት ዕድሎች የነበሩን ቢሆንም አንድ ጎል ብቻ ነበር ያስቆጠርነው። በሁለተኛው አጋማሽ ተጋጣሚያችን አቻ ከሆነ በኃላ አንድ ተጨዋች ወጥቶብን ስለነበረም ጨዋታው ከባድ ነበር። ሆኖም የተጨዋቾቼ የዐዕምሮ ጥንካሬ ልዩ ነበር። በዚሁም መቀጠል አለበት። 

አሰልጣኝ ምንተስኖት ጌጡ – ፋሲል ከተማ

ከጨዋታው አንፃር ጊዮርጊስ ማሸነፍ ይገባው ነበር። እኛ ከወልዋሎው ጨዋታ የተሻለ ኳስ ይዘን ለመንቀሳቀስ ሞክረናል። ረጃጅም ኳሶችን ስለሚጠቀሙም መስመሮችን ለመዝጋት ሞክረን ነበር። ሆኖም ባሰብነው መንገድ አልተጫወትንም። ኳሱንም ይዘው ሲጫወቱ የነበሩት እነሱ ናቸው። ከዚህ በፊት ወደምንታወቅበት አጨዋወት ገና አልተመለስንም። ከጨዋታ ጨዋታ ይህን ችግራችንን እንደምንቀርፍ አስባለው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *