ባምላክ ተሰማ ወደ ዓለም ዋንጫ ያመራል

ኢትዮጵያዊው የፊፋ ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ሩሲያ በያዝነው አመት በምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ላይ ጨዋታዎችን ከሚመሩ አርቢትሮች መካከል ስሙ ተካቷል፡፡

ዛሬ ፊፋ በዓለም ዋንጫው የሚመሩ አርቢትሮችን ይፋ ሲያደርግ በዝርዝሩ ውስጥ 36 የመሃል ዳኞች እና 63 ረዳት ዳኞች ተካተዋል፡፡ የተመረጡት አርቢትሮች በያዝነው ወር ላይ ለሁለት ሳምታት ያህል የሚቆይ ስልጠና በጣሊያን እግርኳስ ማህበር የቴክኒክ ማዕከል ኮቨርሲያኖ ሚሰጥ ሲሆን በስልጠናው ላይ በዓለም ዋንጫ የሚተገበረው VAR ያጠቃልላል፡፡ ፊፋ ላለፉት አራት ሶስት ዓመታት በእግርኳስ ጨዋታን የማንበብ ብቃት የተሻሉ ናቸው ያላቸውን ዳኞች መርጦ የማዘጋጃ ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ የተመረጡት አርቢትሮች በሁለት ቡድኖች ተከፍለው ኮቨርሲያኖ ላይ ስልጣና የሚሰጣቸው ይሆናል፡፡ ከዚህ ሴሚናር በኃላም በVAR ላይ የሚመደቡ ዳኞች የሚታወቁ ይሆናል፡፡ ዓለም ዋንጫው ከመጀመሩ 10 ቀናት በፊት ደግሞ የመጨረሻ ሴሚናር ሞስኮ ላይ እንደሚሰጥ ፊፋ አስታውቋል፡፡

ባምላክ ከአፍሪካ ዞን ከተመረጡ 6 አርቢትሮች መካከል አንዱ ሲሆን የጋምቢያው ባካሪ ፓፓ ጋሳማ፣ የግብፁ ጋሃድ ግሪሻ፣ የዛምቢያው ጃኒ ሲኪዛዊ፣ የሴኔጋሉ ማላንጋ፣ ዴዴሆ እና የአልጄሪው መሃዲ አብዲ ሸሪፍ ሌሎች አፍሪካን የወከሉ የመሃል ዳኞች ናቸው፡፡ ባምላክ በ2017 የካፍ ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ የመጀመሪያ ጨዋታን ካይሮ ላይ አል አህሊ እና ዋይዳድ ካዘብላንካ መካከል መምራቱ ይታወሳል፡፡ ከቻምፒየንስ ሊጉ ፍፃሜ መልስ ሞሮኮ ባስተናገደችው የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) ላይ የተሳፈተ ሲሆን ከፊታችን ባለው የካፍ ቶታል ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ወደ ምድብ ለመግባት የዛምቢያው ዛናኮ እና የሞሮኮው ራጃ ካዛብላንካ የሚያደርጉትን ጨዋታ ይመራል፡፡
የኢትዮጵያ ዳኞች ባለፉት ጥቂት አመታት በአህጉራዊ ውድድሮች ያላቸው ተሳትፎ እየጠነከረ መጥቷል፡፡ ባምላክም በእነዚህ አመታት የአፍሪካ ዋንጫ፣ የክለቦች ውድድሮች እና የማጣሪያ ጨዋታዎች መርቷል፡፡ ከዚህም ባለፈ ህንድ ባስተናገደችው የፊፋ የዓለም ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ መሳተፉ አይዘነጋም፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *