ኮንፌድሬሽን ዋንጫ | ወላይታ ድቻ የመጨረሻ ልምምዱን ዛሬ አከናውኗል

በኦምና ታደለ እና ቴዎድሮስ ታከለ


በአፍሪካ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ እየተሳተፈ የሚገኘው ወላይታ ድቻ ከያንግ አፍሪካንስ ጋር ከሚጠብቀው ከነገው የመጀመርያ ጨዋታ በፊት ዛሬ ሶስተኛ እና የመጨረሻ ልምምዱን ጨዋታውን በሚያደርግበት ዳሬ ሰላም ናሽናል ስታዲየም ሰርቷል፡፡

ወላይታ ድዎች ባሳለፍነው ዕሁድ ወደ ስፍራው ካቀኑ በኋላ ከስታዲየሙ በ3 ደቂቃ ርቀት ላይ በሚገኘው ቤስት ዌስተርን ሆቴል መቀመጫቸውን ያደረጉ ሲሆን የመጀመሪያ ልምምዱን በተጓዘበት እለት አመሻሽ ያደረገ ሲሆን ትላንትናም የወጣቶች ማሰልጠኛ ሜዳ ላይ አከናውኗል። ዛሬ ደግሞ ጨዋታው በሚደረግበት ስታዲየም ቀን 10 ሰአት ላይ ለአንድ ሰአት ከሰላሳ የፈጀ ልምምድን አድርገዋል። በልምምዱ አሰልጣኝ ዘነበ በነገው ጨዋታ ሊጠቀሙባቸው ያሰቧቸውን ተጫዋቾች የለዩ ሲሆን በቅጣት በጨዋታው ላይ በማይኖሩት ተክሉ ታፈሰ እና እሸቱ መና ምትክ ሙባረክ ሽኩር እና ያሬድ ዳዊትን እንደሚጠቀሙ ይጠበቃል፡፡

ወላይታ ድቻ ወደ ታንዛንያ ካመራ ጀምሮ ችግር እየገጠመው ይገኛል የሚሉ መረጃዎች ቢሰሙም የተፈጠረ ችግር እንደሌለ ከስፍራው ያገኘነው መረጄ ያመለክታል። አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀም ዛሬ ከመጨረሻ ልምምዳቸው በኃላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ይህንኑ አረጋግጠዋል።  ” የተለየ ያጋጠመን ችግር የለም። ቢሆንም ግን በምግብ ዙሪያ የለመድነውን ማግኘት አልቻልንም። በካይሮ ብዙ አማራጭ አግኝተን ነበር። እዚህ ግን የፈለግነውን ምግብ መመገብ አልቻልንም ነበር። ሆኖም ከመጣንበት ጊዜ ይልቅ አሁን ላይ የተሻለ ነው።”

በተያያዘም ክለቡ ከመቶ በላይ ደጋፊዎች ወደ ስፍራው ለማቅናት አስበው የሆነ ቢሆንም በወቅቱ የወረቀት ጉዳዮች ባለመጠናቀቃቸው ሳይጓዙ እንደቀሩም ሰምተናል፡፡

ነገ 10:00 ላይ የሚደረገውን ጨዋታ የሚመሩት ናይጄሪያዊያን ሲሆኑ በመሀል ዳኝነት ፈርዲናንድ አኒቴ እንዲሁም ረዳቶቹ አቤል ባባ እና ኢሳ ኡስማን ናቸው፡፡

ኃይማኖት ወርቁ

” ብዙም ያገጠመን ችግር የለም። በጣም ጥሩ ስሜት ላይ ነው ያለነው። በጣም በሚያስደስት ሁኔታ ላይ ለነገው ጨዋታ ተዘጋጅተናል፡፡ ማንም ቡድን ይግጠመን ያለንን ለማውጣት ተዘጋጅተናል። ለወላይታ ድቻም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥሩ ነገርን ለመስራት ነው ወደ ታንዛኒያ የሄድነው። ከፈጣሪ ጋር እናሸንፋለን። ”

በዛብህ መለዮ

” መዘናጋት አያስፈልግም። አሁን ላይ ጨዋታው ሊከብደን ይችላል። አንድ ዙር በተሻገርክ ቁጥር ከበድ ያለ ቡድን ይገጥምሀል። ለዛም በሚገባ ተዘጋጅተናል። ለማሸነፍም ወደ ሜዳ እንገባለን። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *