ኮንፌድሬሽን ዋንጫ | ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ካራ ብራዛቪል የመጨረሻ ልምምዳቸው አድርገዋል

በካፍ ቶታል ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ካራ ብራዛቪል ለሚያደርጉት ወሳኝ የአዲስ አበባ ስታዲየም ፍልሚያ የመጨረሻ ልምምዳቸው አድርገዋል፡፡

ፈረሰኞቹ በቻምፒየንስ ሊጉ በዩጋንዳው ኬሲሲኤ ተሸንፈው ከወደቁ በኃላ ትኩረታቸው ወደ ኮንፌድሬሽን ዋንጫው ምድብ ድልድል ለመግባት በሚደረገው የመጨረሻ ጨዋታ ላይ ሆኗል፡፡ በዚህም መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬ ቦሌ አከባቢ በሚገኘው የልምምድ ሜዳው የመጨረሻ ዝግጅቱን አከናውኗል፡፡ ክለቡ ከካራ ጋር በሚያርገው ጨዋታ አስቻለው ታመነ በቅጣት እንዲሁም አማራ ማሌ እና ታደለ መንገሻን በቅጣት ምክንያት እንደማያሰልፍም ተረጋግጧል።

በኮንፌዴሬሽን ዋንጫው የጋናውን አሻንቲ ኮቶኮ እና የቱኒዚያውን ቤንጎርዳን በማሸነፍ ለዚህ ጨዋታ ከደረሰው የኮንጎ ሪፐብሊኩ ካራ ብራዛቪል በበኩሉ ከ10፡00 ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታድየም ልምምዱን ሰርቷል፡፡ ከሜዳው ውጪ የደርሶ መልሱን የመጀመሪያውን ፍልሚያ ለማድረግ ነገን እየጠበቀ የሚገኘው ካራ የዛሬው የመጨረሻ ልምምዱ በብዛት የቅጣት ምቶች አጠቃቀም ላይ ያተኮረ እንደነበር ተስተውሏል።

ጨዋታው ነገ 10:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም የሚደረግ ሲሆን ጨዋታውን ግብፃዊያን ዳኞች እንደሚመሩት ይጠበቃል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በልምምድ ስፍራው ተገኝተን የቡድኑን ወቅታዊ መረጃዎች እንድናቀርብ ባለመፍቀዱ እና አስተያየቶች እንዲሰጡን ያደረግነው ጥረት ባለመሳካቱ ዘገባዎችን ልንሰራ አልቻልንም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *