“ወደ ምድብ ድልድል የምንገባበትን መሰረት ጥለን እንመለሳለን ” አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሃ 

በካፍ ቶታል ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የመጀመሪያ ተሳትፎውን እያደረገ ይገኛል፡፡ ዛሬ በ10፡00 ሰዓት የታንዛኒያውን ያንግ አፍሪካንስን ዳሬ ሰላም ላይ ይገጥማል፡፡ የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሃ በጨዋታው ዙሪያ ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጡትን አስተያየት እንዲህ አቅርበንላችኋል፡፡

ስለወቅታዊ አቋም

“ጥሩ ነው ያለው፤ በቀደም ከመከላከያ ጋር ስንጫወት ልጆቼ ትንሽ ጥሩ አልነበሩም፡፡ እንግዲህ ያንን ተነጋግረን ሰርተናል፡፡ ብዙ መሻሻሎች እና ትንሽ ግድፈቶችን ለማረም እየጣር ነው በባለፈው ጨዋታ ጥሩ ስላልነበርን፡፡ ይህንን ወደ ነበረበት ለማምጣት ከሞላ ጎደል ሰርተናል፡፡ አሁን ላይ ሁሉም ነገር ጥሩ ነው፡፡”

ዛማሌክን ከውድድር ካስወጡ በኋላ ስላለው ጫና

“ከዛማሌክ በኃላ ብዙ ክለቦች በእኛ ላይ ትኩረት ሰጥተው እንደሚመጡ እናውቃለን፡፡ ሁሉም በጥሩ መልኩ ተዘጋጅቶ እንደሚመጣ ነው እኛም እየተረዳን ያለነው፡፡ ሳንዘናጋ ያለንን ነገር አጠንክረን የእነሱንም ጠንካራ ጎን እየመከትን በራሳችን ጠንካራ ጎን ደግሞ የእራሳችንን ነገር ይዘን ገብተን ሜዳ ላይ ጥሩ ነገር ሰርተን ለመውጣት ነው፡፡ በስነ-ልቦናም ልጆቹን አዘጋጅተን እየሰራን ነው ያለነው፡፡”

ስለተጋጣሚያቸው ያንጋ ያላቸው መረጃ

“አዎ ደርሶናል፡፡ በዚያ ዙሪያም እያየን እየተወያየን ነው ያለነው፡፡ ስለያንጋ መረጃው አለን፡፡ በሜዳቸው እነሱ ልምድ አላቸው፡፡ እያየን ነበር ጠንካሮች ናቸው፡፡ በተክለ ሰውነት በተለይ ጥሩ ናቸው፡፡ ጉልበት ላይ ያመዘነ ጨዋታ ነው የሚጫወቱት፡፡ ያንንም በደንብ ተረድተናል፡፡ በተቻለ መጠን እኛ ቴክኒካሊ በልጠን በእራሳችን መስመር ውጤት ይዘን ለመውጣት ያለንን ሁሉ አሟጣን እንመለሳለን ብለን ተዘጋጅተናል፡፡”

የተክሉ እና እሸቱ በጨዋታው ላይ አለመኖር

“ባሉ ተጫዋቾች ላይ ነው እየሰራን የነበረው፡፡ ባሉን ተጫዋቾች ላይ ተመርኩዘን የሁለቱን ክፍተት ለመሙላት ነው የሰራነው፡፡ ይስተካከላል ብዬ ተስፋ አደርጋለው፡፡”

የመጀመሪያ ጨዋታ እቅድ

“እኛ ወደ ምድብ ድልድል ለመግባት ምዕራፍ የምንከፍትበት ነው ብለን ነው የምናስበው፡፡ ከሜዳ ውጪ እንደመጫወታችን መጠን ውጤት ይዘን ለመምጣት ነው፡፡ ወደ ምድብ ድልድል የምንገባበትን መሰረት ጥለን ነው እንመጣለን ብለን ነው እየተነጋገርን እና እየሰራን ያለነው፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *