” አሁን የበለጠ ወደቤቴ እንደመጣሁ ነው የተሰማኝ ” የካራ ብራዛቪሉ አሰልጣኝ ሮጀር ኤሊ ኦሲዬት 

የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሁለተኛ ዙር የመጀመርያ ጨዋታዎች ከትላንት ጀምሮ እየተካሄዱ ይገኛሉ። ዛሬ ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል ደግሞ አአ ስታድየም ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ካራ ብራዛቪል ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ የሚጠበቅ ነው። አምና በቅዱስ ጊዮርጊስ በደርሶ መልስ ተሸንፎ የወደቀው ሌዎፓርድስን ይዘው ወደ አዲስ አበባ የመጡት አሰልጣኝ ሮጀር ኤሊ ኤሲዮት ዘንድሮም በድጋሚ ሌላኛውን የኮንጎ ቡድን ይዘው መጥተዋል። ከአሰልጣኙ ጋር በጨዋታው ዙርያ ያደረግነውን ቆይታ እነሆ። 

አምና ከሌዎፓርድ ጋር መጥተው ነበር። ዘንድሮ ደግሞ ከካራ ጋር ተመልሰው መጥተዋል።

አሁን የበለጠ ወደቤቴ እንደመጣሁ ነው የተሰማኝ። ምክንያቱም ለሁለተኛ ጊዜ መመለሴ ነው። አምና ከኤ.ሲ. ሌዎፓርድ ጋር ነበር የመጣሁት አሁን ደግሞ ተመልሼ ከካራ ብራዛቪል ጋር መጥቻለሁ ስለዚህ ወደ ቤቴ ነው ተመልሼ የመጣሁት፡፡

ጊዮርጊስን በመጠኑ ያውቁታል ዝግጅትዎ ምን ይመስላል ?

የአምናውን ቅዱስ ጊዮርጊስን አውቀዋለሁ፤ ዘንድሮ ያደረጉትን ለውጥ ግን አላውቅም፡፡ ለውጥም ካለ ምን አይነት ለውጥ እንደሆነ ነገን መጠበቅ ይጠይቃል፡፡  እኛጋ ያለውን ለውጥ ከሆነ ደግሞ ነገ ሜዳ ላይ ታዩታላችሁ ዝም ብሎ በተግባር ማሳየትን እመርጣለሁ፡፡

ምን አይነት ጨዋታ እንጠብቅ ?

የጨዋታ ስትራቴጂያችንን በሚመለከት ተዘጋጅተን የመጣንበት ጨዋታ አለን፤ ባልደረባዬ ደግሞ የተሻለ ጨዋታ የማንበብና የመቀየር ብቃት አለው፡፡ ምን አይነት ጨዋታ ይዘን እንደምንገባ እንነጋገራለን። ስለዚህ ዝም ብለን ነገን ብንጠብቅና ብናይ ይሻላል፤ ጥሩ የተጫወተና የበለጠ ያሸንፍ፡፡
ዘንድሮ ከሜዳ ውጭ ሁሉንም ጨዋታዎች ተሸንፋችኋል፡፡ ይህ በነገው ጨዋታ ላይ ተጽእኖ አይኖረውም ?

የሆነው ሁሉ የሆነው ለበጎ ነው። እኛም ከሁሉም ጨዋታዎች ትምህርት ወስደናል፤ ሁሉም ጨዋታ እኛን የበለጠ እንድንዘጋጅ ነው ያደረገን ስለዚህ ዛሬም የበለጠ ተዘጋጅተን ነው የመጣነው። መርሳት የሌለብህ ነገር ደግሞ አዲስ አበባ ነው ያለነው። አዲስ አበባ የሁላችንም ዋና ከተማ ናት ፤ የአፍሪካ ህብረት መዲና ናት። ስለዚህ እንደውጪ ጨዋታ አንቆጥረውም፤ የምንፈልገው ነገር ስፖርታዊ ጨዋነት ብቻ ነው። ቅድም እንዳለኩህ የተሸለው ቡድን ያሸንፍ፡፡

ኩማሲ ላይ ከኮቶኮ ጋር ስለነበረው ጨዋታና በአንድ ጨዋታ አምስት ፍጹም ቅጣት ምት ስለሰጡት ሴኔጋላዊ ዳኛ ምን ይላሉ ?

እኔ በግሌ በጣም ነው ያዘንኩት ምክንያቱም እኛም በዓለም አቀፍ እግር ኳስ የተሻለ ቦታ መድረስ እንፈልጋለን፡፡  ሁሌም አፍሪካ ውስጥ ብቻ መጫወት አንፈልግም፡፡ ዓለም ዓቀፍ ውድድሮች ላይ የተሻለ ውክልና ለማግኘት ደግሞ የዓለም ዋንጫን የመሳሰሉ ውድድሮችን መምራት የሚችሉ የተሻሉ ዳኞች ያስፈልጉናል፤ ኩማሲ ላይ የሆነው ግን ከዚ በጣም የተለየ ነው፡፡ ዳኛ  ሚዛናዊና የማያደላ ነው መሆን ያለበት ኩማሲ ላይ ያጫወተን ዳኛ ግን ሙሉ በሙሉ የነሱ ደጋፊ ነበር፡፡ እንደዚ ደግሞ ጥሩ አይደለም፡፡ ዳኛ ክለብ ሊወድ ይችላል እንደዚህ አይን ያወጣ ድጋፍ ግን ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም፡፡ ኩማሲ ላይ ግልጽ በደል ነው የተፈጸመብን  ነገ የሚያጫውቱን ዳኞች እንደዛ እንደማይሆኑ ተስፋ አደርጋለው ስህተት ከሆነ ስህተት ካልሆነ ደግሞ አይደለም ዘላለም አንድ ወይም ሁለት ሃገራት ብቻ ማሰብ በፍጹም ተገቢ አይደለም፡፡

እንደውም ዳኛው ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሰለነበር ለናንተ አድልቷል ነበር የተባለው ?

በርግጥ ዳኛው ሴኔጋላዊ ነው፡፡ በፍጹም ግን ለኛ አድልዎ አልነበረም፡፡ አራት ፍጹም ቅጣት ምት የተሰጠው እኛ ላይ ያሸነፉት እነሱ እንዴት ነው ለኛ ያደላው በፍጹም ውሸት ነው፡፡

ሜዳ ላይ የሸኑ ተጫዋቾችም እንደነበሩ ነው የሰማነው። ከጨዋታው በፊት ልምምድ ለመስራት ፍቃደኛም እንዳልነበራችሁ የጋና ሚዲያ ጽፏል ?
ይሄ በፍጹም ከእውነት የራቀ ነው፡፡ ያሸነፈው የትኛው ክለብ ነው ? እነሱ እንዲያሸንፉ ነው የኛ ልጆች የሚሸኑት? ያሸነፉት እኮ እነሱ ናቸው፡፡ ለማን ነው የሚሸኑት ታዲያ ? እንደውም እኛ በካሜራ ያስቀረነው ብዙ በደል ደርሶብናል።

ስለ አዲስ አበባ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊስ ምን ሀሳብ አልዎት ?

ደጋፊውን በሚገባ አውቀዋለው። ምርጥ ድባብ ነው ያለው ነገር ግን ድጋፉ ለኛም ነው። የአፍሪካ ደጋፊ ነው ፤ ወንድማማቾች ነን። ለጊዮርጊስ ብቻ ሳይሆን ለኛም ነው፡፡ ደጋፊው ለኛም ብርታት ነው። ነገ አፍሪካዊ በዓል ነው፤ እኛም የአፍራካ መዲና ላይ ነን። በፍጹም ባይተዋርነት አይሰማንም።

ያለፉትን ሁለት ሶስት ቀናት ዝናብ እየጣለ ነበር ሜዳውን እንዴት አገኛችሁት ?

ሜዳውን አየነው ፤ ተበላሽቷል። አሁን እራሱ ጥሩ አይደለም። ከዚህ በኋላ ከዘነበ ደግሞ የባሰ ይበላሻል፤ በጨዋታው እለት ከዘነበ ደጋፊም ላይኖር ይችላል። ይህ ደግሞ እኛንም ደስ አይለንም፣ ስለዚህ ባይዘንብና በሙሉ ደጋፊ ፊት ብንጫወት ይሻለናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *