” ከፋሲል ከተማ ጥያቄው ሲመጣልኝ በጣም ጥሩ ስሜት ነው የተሰማኝ ” መሳይ ተፈሪ

ትላንት አሰልጣኝ ምንተስኖት ጌጡን ያሰናበተው ፋሲል ከተማ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት በፕሪምየር ሊጉ እና በጥሎ ማለፉ ላሉበት ጨዋታዎች ለረጅም አመታት በወላይታ ድቻ የቆየው አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን ሾሟል፡፡ ዛሬ ወደ ጎንደር ያመራው አሰልጣኝ መሳይ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት ስለ አዲሱ ክለቡ ሹመት የሚከተለውን ብሏል።

” ከክለቤ ጋር ከተለያየው በኃላ ለራሴ እረፍት መስጠትን ስለፈለኩ እንጂ በቅድሚያ ብዙ ክለቦች እየጠየቁኝ ነበር። ጊዜ መውሰድ እና ቆም ብዬ የነበረኝን ጉድለት መፈተሽ የምችልበት ጊዜ ነበረኝ። ለራሴም ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቤም ጊዜን መስጠትን መርጫለው። ከፋሲል ከተማ ጥያቄው ሲመጣልኝ በጣም ጥሩ ስሜት ነው የተሰማኝ። ጥሩ ነገር ልሰራ እንደምችል ሳስብ በደስታ ፍቃደኛ ሆኛለሁ። ፍቃደኛም የሆንኩት ረጅም ጊዜ በአንድ ክለብ እንደማሳለፌ እስቲ ራሴን ወጣ ብዬ ደግሞ በአዲስ ፈተና ልመልከተው በማለት ነው። የደረጃ ሰንጠረዡን ስትመለከት ከ1ኛ እስከ 9ኛ ድረስ ያሉ ክለቦች ለዋንጫ የመፎካከር ዕድል አላቸው። ሁለተኛ ዙር እንደመሆኑ መጠን እያንዳንዱ ቡድን ላለመውረድ አልያም ለሻምፒዮንነት ነው የሚጫወተው። ይህም ከአሁን በኃላ የሚኖሩትን ጨዋታዎች ከባድ ያደርጋቸዋል። ስለዚህ አመቱን በስኬት ለመጨረስ ጠንክሮ በአንድነት መስራትን ይጠይቃል። ከኔ በፊት የነበሩት አሰልጣኞች ጥሩ ነገርን ሰርተው ነው የሄዱት። በዛ ላይ መጨመር ያለበትን በኔ በኩል በማድረግ ቡድኑ ከሻምፒዮንነት ፉክክሩ እንዳይወጣ ያለንኝን ሁሉ እሰጣለሁ፡፡ ፋሲል እንደወላይታ ድቻ ሁሉ ብዙ ደጋፊዎች ካሏቸው ክለቦች መሀከል አንዱ ነው። በዚህ ውስጥ መገኘት እድለኝነት ቢሆንም ደጋፊው ውጤት በመጣ ቁጥር እንደሚያበረታታ ሁሉ ውጤት ሳይኖር ሲቀር ደግሞ ይጠይቃል። ይህ እንደሚያጋጥመኝም አስባለው። በድቻ በብዙ ደጋፊዎች ውስጥ የመስራቱ ልምድ ስላለኝም ከደጋፊዎች ጋር ሚያግባቡት ጥሩ ስራ እና ውጤት መሆናቸውን ጠንቅቄ አውቃለው። ጥሩ ደጋፊ እና አመራር ባለበት ስራዬን መስራት መቻሌም በተመሳሳይ ደስ የሚል ስሜት እንዲሰማኝ አድርጓል። ከእግዚአብሔር ጋር እና ከክለቡ ሌሎች አካሎች ጋር በመሆን መልካም ነገርን ስለመስራት አስባለው። ”

በ19ኛው ሳምንት ፋሲል ከተማ ከወልድያ ጋር በሚያደርገው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ አሰልጣኝ መሳይ ለመጀመሪያ ጊዜ ቡድኑን የሚመራ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *