ሪፖርት | ወላይታ ድቻ በታንዛንያ ሽንፈት ገጥሞታል

በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የምድብ ድልድል ውስጥ ለመካተት ከታንዛንያው ያንግ አፍሪካንስ ጋር ከሜዳው ውጪ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ወላይታ ድቻ በሁለቱ አጋማሾች መጀመሪያ በተቆጠሩበት ግቦች 2-0 ተረቷል።

ጨዋታው በተጀመረ በ28ኛው ሰኮንድ ላይ የግራ መስመር ተከላካዩ ምውኒይ ሀጂ ወደ ግብ ያሻማው ኳስ በፊት አጥቂው ራፋዬል ዳውድ ተገጭቶ ወደ ግብ ተቀይሯል። ሆኖም ወላይታ ድቻዎች ሁኔታው ሳይረብሻቸው ኳስን ከግባቸው ጀምረው መስርተው ለመጫወት ድፍረቱ ነበራቸው። ይህን ለማድረግ ግን የተከላካይ መስመራቸው ወደ መሀል ሜዳ በጣም ይጠጋ የነበረ በመሆኑ ለመልሶ ማጥቃት መጋለጣቸው አልቀረም። ሁኔታውን በመጠቀም ቀጣይ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉትም ባለሜዳዎቹ ነበሩ። 5ኛው ደቂቃ ላይ ለኢማኑኤል ማርቲኒ የደረሰው ኳስ ዉደ ሙከራነት ከመቀየሩ በፊት በሙባረክ ሽኩር ጥረት ሲከሽፍ ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ ደግሞ ግብ አስቆጣሪው ራፋኤል ዳውድ በመልሶ ማጥቃት ነፃ ሆኖ ሳጥን ውስጥ ቢገኝም ሙከራው በግቡ አናት የወጣ ነበር። የ15ኛው እና የ16ኛው ኢብራሂም አጂቡ የርቀት ሙከራዎችም እንዲሁ ተጠቃሽ ነበሩ።

ወላይታ ድቻዎች በመጀመሪያው አጋማሽ አብዛኛው ደቂቃዎች ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥርን ይዘው ከመታየት ባለፈ በተጋጣሚያቸው ሳጥን ውስጥ የመገኘት አጋጣሚዎችም ነበሯቸው። ሆኖም ቡድኑ በተለይ መሀል ሜዳ ላይ ከተጋጣሚው የበረከተ ጫና ባይደርስበትም የማጥቃት ፍጥነቱ የሚፈለገውን ያህል አልነበረም። በድቻ የዘገዩ ቅብብሎች ምክንያት የመከላከል ቦታቸውን ለመያዝ እምብዛም ያልተቸገሩት ያንግ አፍሪካንሶች የጦና ንቦችን ጥቃት መመከት ሲከብዳቸው አልታየም። ይህም በመሆኑ 41ኛው ደቂቃ ላይ ጃኮ አራፋት ከኃይማኖት ወርቁ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ አውርዶ ለበዛብህ ሰጥቶት በዛብህ ከቅርብ ርቀት አክርሮ ከሞከረው እና ግብ ጠባቂው ዮውዝ ሮስታንድ ካዳነበት ሙከራ ውጪ ሌላ አጋጣሚ መፍጠር አልቻሉም።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር የተሻለ መነቃቃት ያሳዩት ያንግ አፍሪካንሶች ቢሆኑም በሙከራ ቀዳሚ የነበሩት ግን ወላይታ ድቻዎች ሆነዋል። 53ኛውደቂቃ ላይ በዛብህ መለዮ ከሳጥን ውስጥ ያደረገው ሙከራ ግን ኢላማውን ቢጠብቅም ጎል መሆን አልቻለም። ይልቁንም ከአንድ ደቂቃ በኃላ ኳስ እና መረብን ማገናኘት የቻሉት ያንጋዎች ነበሩ። ጎሏ የተቆጠረችበት መንገድ እንደመጀመሪያው ሁሉ ከግራ መስመር በተሻገረ ኳስ በግንባር ተገጭታ ሲሆን ግብ አግቢው ግን ሁለተኛው ቋሚ ላይ ነፃ ሆኖ ቆሞ የነበረው ኢማኑኤል ማርቲኒ ነበር። ተጋጣሚያቸው ተሻጋሪ ኳስን በአግባቡ የመከላከል ችግር እንዳለበት ያስተዋሉት ያንግ አፍሪካንሶች 61ኛው ደቂቃ ላይ ተመሳሳይ መልክ ከነበራት አጋጣሚ ግብ ለማስቆጠር ቢቃረቡም የዩሱፍ ሙሀይሉ የግንባር ክስ በማይታመን መልኩ በጎን ወደ ውጪ ወጥቷል።

እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ አሁንም በእርጋታ ተሞልተው እና በኳስ ቁጥጥር ላይ ተመስርተው የተንቀሳቀሱት ወላይታ ድቻዎች 73ኛው ደቂቃ ላይ በዛብህ መለዮ ከሳህን ጠርዝ ላይ በቀጥታ በመታው ኳስ አንድ ግብ ለማግኘት ቢቃረቡም ዮውዝ ሮስታንድ መረቡን አላስደፍር ብሏል። ቡድኑ ሀሳቡን ማጥቃት ላይ በማድረጉ ከኃላ ይተው በነበረው ክፍተት እና አልፎ አልፎ በአደገኛ ሁኔታ በሚሰራቸው የቅብብል ስህተቶች ለመልሶ መጠቃት በእጅጉ ክፍት ቢሆንም ኢብራሂም አጂቡ ካደረጋቸው ሁለት ሙከራዎች ውጪ ሶስተኛ ግብ ለማስተናገድ የቀረበባቸው ወቅቶች በቁጥር በርካታ አልነበሩም። ሆኖም የኢብራሂም የ73ኛ ደቂቃ የሳጥን ውስጥ ሙከራ የወንደሰን ገረመውን ቅልጥፍና የፈለገች ነበረች። 

ወላይታ ድቻዎች በተጋጣሚያው የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ዙሪያ መጠነኛ ነፃነት የነበራቸው ቢሆንም ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ጃኮ አራፋት ወደ እነ አብዱልሰመድ አሊ እየቀረበ እና ወደ መስመር እየወጣ ቅብብሎችን ለማቀላጠፍ ይሞክር የነበረበት የጨዋታ ሂደት ፊት ላይ ዕድሎችን መጠቀም የሚችል ሁነኛ ተጨዋች እንዳይኖር አድርጓል። በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች የተደረጉት ሶስት ሙከራዎችም ዮውዝ ሮስታንድን የፈተኑ አልነበሩም። ወላይታ ድቻም የግብ ልዩነቱን ለማጥበብ ሌላ ዕድል ሳያገኝ ጨዋታው እንዲጠናቀቅ ሆኗል።

ሁለቱ ቡድኖች የመልስ ጨዋታቸውን ከ11 ቀናት በኋላ በሀዋሳ አለምአቀፍ ስታድየም ያካሂዳሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *