አርባምንጭ ከተማ በውድድር አመቱ ለሁለተኛ ጊዜ አሰልጣኝ አሰናበተ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዘንድሮ ደካማ የውድድር ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘውና በወራጅ ቀጠናው ውስጥ የተቀመጠው አርባምንጭ ከተማ አሰልጣኝ እዮብ ማለን ማሰናበቱ ታውቋል። የአርባምንጭ ከተማ ቦርድ ክለቡ በወልዋሎ 3-0 መሸነፉን ተከትሎ ትላንት ምሽት ተሰብስቦ ውሳኔውን እንዳሳለፈ የታወቀ ሲሆን አሰልጣኙ የተሰጣቸውን እድል በአግባቡ አለመጠቀማቸው ለውሳኔው ምክንያት መሆኑ ተገልጿል። 

አሰልጣኝ እዮብ ማለ ሀዲያ ሆሳዕናን ለቀው በፀጋዬ ኪዳነማርያም ምትክ የአርባምንጭ ከተማ አሰልጣኝ ሆነው ከ3 ወራት በፊት የተሾሙ ሲሆን ቡድን ከተረከቡ በኋላ ባደረጓቸው 11 የሊግ ጨዋታዎች 4 አሸንፈው 2 አቻ ወጥተው ፣ 5 ሽንፈት አስተናግደዋል። ክለቡ በተለይ ከሜዳው ውጪ የሚያስመዘግበው ደካማ ውጤት ሲያልመው ከነበረው የወራጅ ቀጠና መራቅን እንዳያሳካ አድርጎታል። ክለቡ በቀጣይ ሌላ አሰልጣኝ የመቅጠር ፍላጎት እንደሌለው የተሰማ ሲሆን ምክትል አሰልጣኙ ማትዮስ ለማ እና ግብ ጠባቂው ጃክሰን ፊጣ እስከ ውድድር አመቱ መጨረሻ ድረስ ቡድኑን ይመራሉ ተብሏል።

አሰልጣኝ እዮብ ማለ በጉዳዩ ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል። ” ውሳኔው አስገራሚ ነው የሆነብኝ። ቡድኑን ለማሻሻል እና ካለበት ደካማ የውጤት ጉዞ ለማውጣት እየጣርኩ ባለበት ጊዜ የስንብት ውሳኔ መምጣቱ አሳዝኖኛል። ክለቡ እዚህ ችግር ውስጥ የገባው በእኔ ምክንያት ከሆነ የአርባምንጭ ህዝብ ይፍረደኝ። ጥሩ ስራ እየሰራሁ ስለነበር ደጋፊው የሚያዝንበት ውሳኔ ነው። ” ብለዋል።