የከፍተኛ ሊግ አጫጭር መረጃዎች እና የዝውውር ዜናዎች

የዝውውር ዜናዎች

የከፍተኛ ሊግ ዝውውር መስኮት የመጀመርያው ዙር ካበቃበት ጊዜ አንስቶ ውድድሩ ከተጀመረ በኃላ ለ21 ቀን ክፍት ሲሆን ክለቦችም እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ።


* ካፋ ቡና 4 ተጫዋቾችን ከቡድኑ ሲያሰናብት 5 ተጫዋቾችን በምትኩ አስፈርሟል። መሀመድ ሙሳ ከከዳባ አፋር ፣ ቶምኪል ፈቱ ጀማል ከ ነገሌ ከተማ ፣ ጆንቴ ገመቹ ከሰሜንሸዋ ደ/ብርሀን፣ ሙሉዓለም በየነ እና ምሳሌው ሸዋፈራው ከመድን ለክለቡ የፈረሙ ተጫዋቾች ናቸው።


* ሀድያ ሆስዕና በአንደኛው ዙር መባቻ ከጅማ አባጅፋር ጋር የተለያየው ዝናቡ ባፋአን ሲያስፈርም በቅርቡም አራት ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ እንደሚቀላቅል አስታውቋል።


* ጅማ አባቡና በክረምቱ የዝውውር መስኮት ካስፈረማቸው ተጫዋቾች መካከል ከብሩክ ጋሻው፣ ስንታየሁ አያሌው እና ቴዎድሮስ ሁሴን ጋር በስምምነት የተለያየ ሲሆን በምትኩም ከሊፋ ዑስማን ከፌደራል ፖሊስ፣ አማኑኤል ጌታቸው ከቤንች ማጂ ቡና፣ ሮባ ወርቁ ከጅማ አባጅፋር እንዲሁም ሁለት ናይጄርያዊያን (ሀኪም አካንዴ እና አብሎዲ) አስፈርሟል።


* የምድብ ለ መሪ ሆኖ የጨረሰው ሀላባ ከተማ ከመቂ መሐመድ ተማም እና የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ አማካይ አድናን ቃሲምን ወደ ቡድኑ መቀላቀል ችሏል።


* ወሎ ኮምቦልቻ ከአሰልጣኝ ለውጥ በተጨማሪ የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ፣ ዳሽን ቢራ እና አውስኮድ አጥቂ አንተነህ ተሻገር ፣ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የተለያየው አብዱሰላም ኑር እና አንጋፋው አሸናፊ ይታየውን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል።


* የካ ክፍለ ከተማ አምስት ተጫዋቾችን ከቡድኑ ሲቀንስ በምትካቸው 5 ተጫዋቹችን ወደ ቡድኑ ተቀላቅሏዋል። እዮብ ተሾመ ፤ አቡበከር ካሚል እና አሸናፊ ካሳ ከአራዳ ክፍለ ከተማ ሲፈርሙ ሀብታሙ ከበደ ከመተሀራ እንዲሁም ደምሰው ቦጋለ ከ አዲስ አበባ ፖሊስ ሌሎች የካን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ናቸው።


አሰልጣኞች ቅጥር

ወሎ ኮምቦልቻ

በምድብ ሀ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ወሎ ኮምቦልቻ በሁለተኛው ግማሽ የውድድር አመት ውጤቱን ለማሻሻል አዲስ አሰልጣኝ መቅጠሩን ለሶከር ኢትዮጽያ ገልጿል። ባለፈው አመት ወልዋሎን ወደ ፕሪምየር ሊግ ያሳደጉት ብርሃኔ ገ/እግዚአብሔርም የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ሆነው ተሹመዋል። አሰልጣኝ ብርሃኔ ከሰኞ ሚያዝያ 16 ጀምሮ ከቡድኑ ጋር ልምምድ የጀመሩ ሲሆን የፊታችን ቅዳሜ በሁለተኛ ዙር የመጀመርያ ጨዋታ ወሎ ኮምቦልቻ ነቀምትን በሚያስተናግድበት ጨዋታ ቡድኑን እየመሩ ወደ ሜዳ የሚገቡ ይሆናል።


ሻሸመኔ ከተማ

ከ15 ቀናት በፊት ከአሰልጣኝ ያሬድ አበጀ ጋር የተለያየው ሻሸመኔ ከተማ የቀድሞው የሀላባ አሰልጣኝ አላምረው መስቀሌን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ቀጥሯል። በ2007 ከሀላባ ጋር ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ ከጫፍ ደርሰው የነበሩት አሰልጣኝ አላምረው በምድብ ለ በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ሻሸመኔን ውጤት የማሻሻል ፈተና ይጠብቃቸዋል።


ነገሌ ከተማ

ከመጋቢት 20 ጀምሮ እገዳ ላይ የነበሩት አሰልጣኝ ነፃነት ገብሬ ሚያዝያ 15 ላይ ከክልሉ ከንቲባ እና ከቦርዱ ጋር ባደረጉት ውይይት ወደ ስራቸው እንዲመለሱ መወሰኑን ሶከር ኢትዮጽያ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። በዚህም መሰረት አሰልጣኝ ነፃነት ያለፉትን ሁለት ቀናት ወደ ቡድኑ ተመልሰው ልምምድ ማሰራት ጀምረዋል።


የውድድር ማራዘም ጥያቄ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አወዳዳሪ አካል የመርሀ ግብር ይራዘምልኝ ጥያቄ እንደማያስተናግድ አስታውቋል። አንዳንድ ቡድኖች የመጀመሪያ ጨዋታቸው እንዲራዘም ጥያቄ ቢያቀርቡም ፌዴሬሽኑ ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ ውድድሩ እንደማይራዘም በደብዳቤ አሳውቀል።


ተዋወቁት 

(በቴዎድሮስ ታከለ)

ስም– ገ/መስቀል ዱባለ

ዕድሜ– 20

የትውልድ ቦታ – ሲዳማ ቡርሳ

ቁመት– 1፡80

ክብደት– 65

የሚጫወትበት ቦታ – አጥቂ

ክለብ – ስልጤ ወራቤ

የቀድሞ ክለብ– ከሀዋሳ ከተማ

– ከሀዋሳ ከተማ በውሰት ለስልጤ ወራቤ እየተጫወተ ይገኛል።

– በከፍተኛ ሊጉ 5 ጎሎች አስቆጥሯል።


” የኳስ አጀማመሬ በትውልድ አካባቢዬ ነው። በሲዳማ ዞን በምትገኘው ቡርሳ ወረዳ በምጫወትበት ወቅት ጥሩ በመንቀሳቀሴ ለሲዳማ ዞን መጫወት ቻልኩ። ዞን ላይ ስጫወት አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ተመልክቶኝ ወደ ሀዋሳ ከተማ ከ17 አመት በታች ቡድን አካተተኝ። በሁለተኛ አመቴ ወደ ተስፋው አደግኩኝ። ዘንድሮ ወደ ዋናው የሀዋሳ ቡድን ባድግም በውሰት መሄድ አለብህ ተብዬ ወደ ስልጤ ወራቤ ተቀላቅያለሁ። በቀጣይ ግን ካገኘሁት ልምድ በመነሳት አሳዳጊ ክለቤን መርዳት እፈልጋለሁ። ሀዋሳ ትልቅ ቡድን ነው። ለኔ እዚህ መድረስ ይስሀቅ ካሳዬ የሚባል እና አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን ላመሰግን እወዳለሁ፡፡