ሙስጠፋ መኪ አሁን ላይ ስላለበት የጤና ሁኔታ ይናገራል…

ፌዴራል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ በወልድያ እና ፋሲል ከተማ ጨዋታ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ይታወሳል። ሙስጠፋ ከህመሙ ሙሉ ለሙሉ ባያገግምም አሁን ህክምናውን ተከታትሎ አዲስ አበባ በእህቱ ቤት በማረፍ ጉዳቱን እያስታመመ ይገኛል። ችግሩ ከተፈጠረ 15 ቀናት ያሳለፈ ሲሆን አሁን ስላለበት ሁኔታ ፣ ስለደረሰበት ጉዳት እና እየተደረገለት ስላለው ድጋፍ እንዲሁም በቀጣይ መደረግ ስለሚገባው ነገር በመኖርያ ቤቱ ዛሬ ማለዳ የተገኘችው ሶከር ኢትዮጵያ ከሙስጠፋ ጋር ያደረገችውን ቆይታ እንዲህ አቅርባዋለች። 

የጉዳቱ ሁኔታ እንዴት ታስታውሰዋለህ ?

የፍፁም ቅጣት ምቱ ከተሰጠበት ሁኔታ ልጀምር። ውሳኔው ተገቢ አይደለም በሚል ተቃውሞ ከወልዲያ ተጨዋቾች እና ከአሰልጣኙ መሀል ተፈጠረ። ከሰጣ ገባው በኋላም እንዲመታ ተደረገ። ከዛ ጎል ገባ ፤ ዋናው ዳኛ ጨዋታውን ሊያስጀምር ሲል ሳይጠበቅ በካታንጋ በኩል ደጋፊዎች ገቡ። ዋናው ዳኛ ለሚ ንጉሴ ራሱን ለማዳን እያፈገፈገ ባለበት ጊዜ የፈለጉት እርሱን ስለነበር ለመርዳት በማሰብ ተዉ እረፉ እያልኩ ባለበት ሰአት ከትሪቡን በኩል የተወሰኑ ተመልካቾች ገቡ። በምን እንደመቱኝ አላወኩም ወደኩ ፤ ከዚህ በኋላ የሆነውን አላቅም። አብረውኝ የነበሩ የስራ ባልደረቦቼ በኋላ እንደነገሩኝ ከሆነ በካሜራ ስታንድ ብረት እንደተመታው ተረድቻለው።

የህክምናህ ሁኔታ እንዴት ነው ?

ወልዲያ እያለው ራሴን ስቼ ስለነበር ህክምናዬ እንዴት እንደነበር አላስታውስም። ጓደኞቼ እንደነገሩኝ ከሆነ ብዙ ደም ፈሶኝ ስለነበር ወልድያ ሆስፒታል እንደደረስኩ አጋጣሚ ዳኞች ቦርሳቸውን ስላልያዙ ክፍያ ካልተከፈለ አናክመውም ብለዋቸው ነበር ። የሆነ የወልድያ ደጋፊ ነው። ማለት ከደጋፊም ጨዋ ደጋፊ አይጠፋም እና አክሙት እንጂ ብር ችግር የለም ብሎ ብር የሰጣቸው። መትረፍ አይተርፍም ግን ዝም ብለን አክመን እንሰፋዋለን ብለው ደሜ እንዲቆም ሰፉኝ። ከዛ እዛው አድሬ ማርፈጃው ላይ በኮንትራት ወደ አዲስ አበባ መጣሁ። ለተሻለ ህክምና ኢትዮ ካናዳ ሆስፒታል ሲቲስካን ከተነሳው በኋላ የጳውሎስ ሆስፒታል ቅርንጫፍ ወደሆነው አቤት ሆስፒታል ሄድኩኝ። መጀመሪያ ያገኘሁት ህክምና በቂ አይደለም ብለው በማመናቸውም የተሰፋሁትን እንደገና ፈተው በድጋሜ በመስፋት ህክምና አድርገውልኛል። አርብ እለተም ራሴን አወቄ ነቃሁኝ። አሁን እህቴ ቤት ነው ያለሁት ። 

የጤንነት ሁኔታ አሁን ጥሩ ነው ?  

ፈጣሪ ይመስገን መትረፉም በቂዬ ነው። ጤንነቴ ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ነው ። በጣም ሰላም ነኝ። ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁን ።

የፌዴሬሽኑ አመራሮች የጤንነትህን ሁኔታ እየተከታተሉ ነው ? 

የፌዴሬሽኑ ሰዎች አልመጡም እንዳይባል ያህል መጥተዋል። ከሞላ ጎደል አንዴ መጥተው ጠይቀውኛል። ከዛ በተረፈ ደግመው አልመጡም። ምንም አይነት ድጋፍ እያገኘው አይደለም። የሙያ ባልደረቦቼ እንደውም ነጋ ጠባ ነው እየመጡ የሚጠይቁኝ። ከክፍለ ሀገር ሁሉ ሳይቀሩ ። አንድም ቀረ የምለው የለም ሦስቴ አራቴ ደጋግመው ጠይቀውኛል ፈጣሪ ይመስገን ።

የህክምናህ ወጪ በማነው የሚሸፍነው? 

የህክምና ወጪዬን ቤተሰቦቼ ናቸው እየሸፈኑ ያሉት። እህቶቼ እና ወንድሞቼ ፤ እኔ ምንም አላወጣሁም። እነሱ ናቸው ወጪውን እያወጡ ያሉት ።

መጨረሻ የምታስተላልፈው መልዕክት አለ  ? 

ለእኔ አይደለም መልክቴን ማስተላለፍ የምፈልገው። ሊግ ውድድር ላይ ለሚያጫውቱት ጓደኞቼ ነው መልዕክቴ። እኔ ተርፌአለው ፈጣሪ ይመስገን ። በጣም ሰላም ነኝ። ግን ከባድ ነው። ሊጎቹ እንዲህ ችግር እየተፈጠረባቸው ማጫወት ከባድ ነው። ስለዚህ የፀጥታ አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል። የፀጥታ አካላት በየሜዳው ሳይኖሩ ጨዋታዎች ቢካሄዱ መልካም ነበር ፤ ሆኖም ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች ግንዛቤ እስኪያገኙ ድረስ በቂ ጥበቃ ኃይል መኖር አለበት።           

ፌደራል ዳኛ  ሙስጠፋ መኪ በትዳር ህይወቱ የአንድ የስድስት ወር ወንድ ልጅ አባት ሲሆን ይህ ባለሙያ አስፈላጊው ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያስፈልገው መጠቆም እንወዳለን።