ቢኒያም በላይ ከስከንደርቡ ጋር የአልባኒያ ሱፐርሊጋን አሸንፏል

ስከንደርቡ ኮርሲ የአልባኒያ ሱፐርሊጋን ማሸነፉን አረጋግጧል፡፡ ኢትዮጵያዊው አማካይ ቢኒያም በላይም በአውሮፓ የመጀመሪያ ዓመት ቆይታው የሊግ ዋንጫ ባለቤት ሆኗል።

ስከንደርቡ በ32ኛ ሳምንት የሊግ ጨዋታ ከሜዳው ውጪ ወደ ኬኤስ ሉሽናን ገጥሞ 4-2 ሲያሸንፍ የዓምና ቻምፒዮኑ ኩኪሲ ከሜዳው ውጪ በቱታ ዱረስ 3-2 መረታቱን ተከትሎ ቀሪ ሶስት ጨዋታዎች እየቀሩት የሊግ ዋንጫውን ወደ ኮርሲ ከተማ መመለሱን አረጋግጧል፡፡ ጋምቢያዊው አሊ ሶዊ ሃትሪክ ሲሰራ ናይጄሪያው ሰገን አድኒ ቀሪዋን አንድ ግብ አክሏል፡፡ በጨዋታው ላይ ቢኒያም በቡድኑ ውስጥ አልተካተተም ነበር፡፡

ቢኒያም በዓመቱ መጀመሪያ በጀርመን ቡንደስሊጋ 2 እና ኦስትሪያ ክለቦች የሙከራ ግዜን ያሳለፈ ሲሆን ወደ ስከንደርቡ ከተዘዋወረ በኃላም በተወሰኑ የሊግ፣ የአልባኒያ ዋንጫ እና የዩሮፓ ሊጋ ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ ችሏል፡፡ ከዚህም አልፎ ስከንደርቡ ለፍፃሜ በደረሰበት የአልባኒያ ዋንጫ ላይ ሁለት ግቦችን ከመረብ አዋህዷል፡፡ ስከንደርቡ ከ2010 ጀምሮ በተከታታይ የአልባኒ ሱፐር ሊጋን ያሸነፈ ሲሆን በ2016/17 በኩክሲ የተቀማውን ክብር ዘንድሮ ዳግም አስመልሷል፡፡

ሆኖም ቡድኑ ከአቋማሪ ድርጅቶች ምክንያት የጨዋታ ውጤቶች የማስለወጥ ስራዎችን ሲሰራ ነበር በሚል በዩኤፋ ተከሶ ጉዳዩ በፍርድ እየታየ ሲሆን በ2016 በዚሁ ጉዳይ ምክንያት ከአውሮፓ ውድድሮች ታግዶ ነበር፡፡

በአልባኒያ ዋንጫ ኬኤፍ ላሲን በያዝነው ወር የሚገጥመው ስከንደርቡ ማሸነፍ ከቻለ ቢኒያም የሁለትዮሽ ዋንጫ ባለቤት ይሆናል፡፡

በ2017 ኢትዮጵያው አማካይ ሰፎኒያስ አስረስ የሚጫወትበት ኤፍሲ ስተምብራስ የሊቱኒያ ዋንጫ ማሸነፉ ይታወሳል፡፡